20 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
20 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ ነው
አሶሳ፣ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተለያዩ አካባቢዎች 20 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
በኮርፖሬሽኑ የአሶሳ ቅርንጫፍ በአሶሳ ዞን አብራሞ ወረዳ በ328 ሄክታር መሬት ላይ እያከናወነ ያለው የድቃይ በቆሎ ዘር ብዜት ሥራ ዛሬ ተጎብኝቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በመስክ ጉብኝቱ ላይ እንዳሉት፣ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በ22 የሰብል አይነቶች 78 ዝርያዎች ላይ ምርምር እያካሄደ ይገኛል።
የምርምር ሥራው እንደአገር ምርታማነትን ለማሻሻል ያለመ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ19 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር እያባዛ መሆኑን አቶ ክፍሌ ጠቁመው፣ ከዚህም ከ407 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ አርሶ አደሮችን እና ባለሃብቶችን አቅም ለማሳደግ በተለያየ መንገድ እገዛ እያደረገ መሆኑንም አቶ ክፍሌ አመልክተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለኮርፖሬሽኑ የልማት ሥራ 1ሺህ 500 ሄክታር መሬት ማስረከቡን ጠቁመው፣ "ይህም የክልሉ መንግስት የግብርና ምርታማነትን በማሻሻል የአርሶ አደሩ ህይወት እንዲቀየር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል" ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተረከበው መሬት ላይ በሙሉ አቅሙ የምርምር ብዜት ሥራውን ለማከናወን ጥናት እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው፣ ለሥራው ውጤታማነት ተጨማሪ መሬት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በቅርቡ የግብርና ሜካናይዜሽን ቅርንጫፍ በክልሉ እንደሚከፈት ያመላከቱት አቶ ክፍሌ፣ ከሰብል ልማት በተጨማሪ በክልሉ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ያለውን እጣን እና ሙጫ ላይም ምርታማነትን ለማሳደግ ምርምር ለማካሄድ መታሰቡን ገልጸዋል።
የመስክ ጉብኝ የተካሂደበት የአብራሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱለጢፍ አፉዲ በበኩላቸው፣ በወረዳው 328 ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በመስክ ጉብኝቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።