ኢትዮጵያዊያን የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያዊያን አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚያመርቱትን ምርቶች የመጠቀም ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጥሪውን አቅርቧል።
ከአንድ መቶ በላይ አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት 'የኛ ምርት' የተሰኘ አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር በመጪው ታህሳስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ኤግዚቢሽንና እና ባዛሩን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከፕራና ኢቨንትስ ጋር በመተባበር የሚዘጋጁት ሲሆን ይህን አስመልከቶ ተቋሙ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ እንዳሉት፤ በአገሪቱ ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ጋር ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶች ይመረታሉ።
ማኅበረሰቡ ለአገሩ ምርት ያለው ዝቅተኛ ግምት ምርቶችን በሚፈለገው መጠን እየተጠቀመ እንዳልሆነ አብራርተዋል።
ይህም አምራች ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ እንዳይሆኑና የሀገርን ኢኮኖሚ በሚፈለገው ልክ እንዳይደግፉ ሆኗል ብለዋል።
ይህንንም ልማድ ለመቀየር ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ በአምራች ኢንተርፕራይዞች የሚመረቱ ምርቶችን የመጠቀም ባህላቸውን ከምንጊዜውም በላይ ሊያሳድጉ ይገባል ብለዋል።
ከታህሳስ 3 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም “ኢትዮጵያ ታምርት፣ እኛም እንሸምት“ በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና በዛር በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ ከ100 በላይ በልዩ ልዩ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራች ኢንተርፕራይዞች ይሳተፋሉ ብለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ በጨርቃ ጨርቅ ፣በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በማዕድንና ጌጣ ጌጥ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዝግጅቱም አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚያመርቷቸውን ምርቶች በማስተዋወቅ የገበያ ትስስርን ማጠናከር፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲጎለበት ማድረግ እንደሆነ አንስተዋል።
በተጨማሪም ኢንተርፕራይዞች ተኪ ምርት የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሳለጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጎልበት ዝግጅቱ ትልቅ ሚና ያለው ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
የፕራና ኢቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ በበኩላቸው ኤግዚብሽንና ባዛሩ የታለመለትን ዓላማ ከግብ እንዲደርስ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ዝግጅቱ ዘርፉ አሁን ያለበትን የእድገት ደረጃ በሚያመላክት እና ቀጣይ በዘርፉ የሚኖሩ መልካም ዕድሎችን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡
በዚህ የሀገር አቀፍ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ከ50ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል።