የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደም ለገሱ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ) ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ''ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ኃሳብ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የወሰዱትን ሥልጠና ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ደም ለገሱ።
የኢትዮጵያ የደምና ኅብረ-ሕዋስ ባንክ አገልግሎት በተለያዩ ጊዜያት የደም ክምችት እጥረት ያጋጥመዋል።
ለዚህም ዜጎች በበጎ ፍቃድ በቋሚነት ደም የመለገስ ባሕል አለመዳበሩ ነው በምክንያትነት የሚጠቀሰው።
ይህንንም ችግር ለማቃለልና ተቋሙም የሚያስፈልገውን የደም ፍላጎት እንዲያቀርብ ሕብረተሰቡ ደምን በቋሚነት መለገስ እንዳለበት በተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቧል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደም በመለገስ የደም እጥረት እንዳይከሰት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የደም ክምችት እጥረት ለመፍታት እያንዳንዱ ዜጋ በበጎ ፍቃደኝነት ደም የመለገስ ባህሉን ሊያዳብር ይገባል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባል አይሻ ሽፋ፤ ደም የሚለግሱት መዳን እየቻሉ በደም እጥረት ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ለመታደግ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል ዶክተር ቤተልሔም ላቀው፤ ደም መለገስ ለሕዝብ ያለንን ወገንተኝነት ያሳያል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሕብረተሰቡ የሚተካ ደምን በመለገስ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቹን መታደግ ይገባል፤ ለዚህም ቁርጠኛ መሆናቸውን ሌላኛው የምክር ቤት አባል ከድር አደም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ባለሙያ ዮሃንስ ከፈለኝ በበኩሉ፤ ተቋሙ ከበጎ ፍቃደኞች የሚሰበሰበውን ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።
በኢትዮጵያ ከወሊድ፣ ከመኪና አደጋና ከሕክምና ጋር ተያይዞ የደም ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም ከበጎ ፍቃደኞች የሚሰበሰበው ግን በቂ አይደለም ነው ያለው።
እንዲህ አይነት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በበጎ ፍቃድ ደም የመለገስ ባህልን ማዳበር እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ ዓመታዊ የደም ፍላጎት አንድ ሚሊዬን ዩኒት ያህል ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ በ2015 ዓ.ም ከለጋሾች የተገኘው ደም ከ353 ሺህ ዩኒት እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ።