ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ  አገልግሎት ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነትን እየፈጠረ ነው 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት መፍጠር የሚያስችል ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ወጣቶች በሀገር ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ላይ ያላቸውን ኃላፊነት መወጣት የሚችሉበት ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት መርሀ ግብር ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

በዚህም በስምንት ዙሮች 50 ሺህ የሚጠጉ በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በማሰልጠን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም  ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ትርክት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

በዚህም ወጣቶች ልዩነታቸውን ውበት አድርገው ሀገራዊ አንድነት ከመፍጠር ይልቅ በክልላቸው ታጥረው እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ  ሲያደርጋቸው ቆይቷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የሰላም ሚኒስቴር ወጣቶች ከአካባቢያቸው ወጥተው ብሔራዊ አንድነት የሚፈጥሩበት የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ከተለያዩ የኒቨርሲቲዎች በተለያየ የሙያ መስክ የተመረቁ መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ከክልላቸው ውጭ በመሰማራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ ኢትዮጵያን በተለያዩ ጉዳዮች በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በራሳቸው ፍላጎት የተመለመሉ   በመሆናቸው በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ውጤታማ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት በወጣቶች ዘንድ አብሮነትን በማጎልበት ለሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በሀገር ግንባታ ሂደት መንግስትና ሀገር የተለያዩ መሆናቸውን መረዳት ይገባል ብለዋል፡፡

የሀገር ግንባታ በሂደት የሚከናወን እንጂ በአንድ ወቅት የሚያልቅ ባለመሆኑ ዜጎች ከልዩነት ይልቅ አንድነትና መግባባትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ አተኩረው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ የእምነት፣ ሙያና አካባቢ የተወጣጡ ቢሆንም ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግና በጋራ መቆማቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የምንፈልጋትን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ቀጣይነት እንዲኖረው እየሰራን ነው፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል፡፡ 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም