ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት ለሚገዙ እቃዎች የሚውል የካርጎ ማዕከል ወደ ሥራ ሊያስገባ ነው

 አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት ለሚገዙ እቃዎች (ኢ-ኮሜርስ) የሚውል የካርጎ ማዕከል በቅርቡ ወደ ሥራ ሊያስገባ  መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ የካርጎ ዘርፉን ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። 

ይህንንም ተከትሎ አየር መንገዱ የካርጎ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ሁለት ዘመናዊ የካርጎ ማከማቻና ማደራጃ ማዕከላትን ወደ ሥራ ማስገባቱን ጠቁመዋል።   

ጎን ለጎንም 16 የጭነት አገልግሎት (ካርጎ) አውሮፕላኖች በሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።   

የዘርፉን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ በመጪው ሰኞ ደግሞ 100 ቶን የመጫን አቅም ያለው ግዙፍ የካርጎ አውሮፕላን ከቦይንግ እንደሚረከብ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መጪው ሁለት ዓመታት ውስጥ አራት የካርጎ አውሮፕላኖችን አየር መንገዱ ተረክቦ ወደ ሥራ ለማስገባት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተጓዳኝም፤ አየር መንገዱ በ50 ሚሊየን ዶላር ያስገነባው ሦስተኛውንና ለኢ-ኮሜርስ (በኦን ላይን የሚገዙ እቃዎችን) የሚውል ዘመናዊ የካርጎ ማዕከል በቅርቡ ወደ ሥራ ያስገባል ብለዋል።

 

ይህም በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓት የሚገዙ እቃዎችን ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በአዲስ አበባ በኩል ለማጓጓዝና የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአጠቃላይ ገቢው ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሰበሰበው ከካርጎ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል የዘርፉን አቅም ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

 

በዚህም የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎት ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት። 

 

ለአብነትም ባለፈው የ2015 በጀት ዓመት ከ730 ሺህ ቶን በላይ እቃ መጓጓዙን ጠቅሰዋል በተያዘው በጀት ዓመትም የበለጠ የካርጎ ጭነት አገልግሎት ለመሥጠት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።  

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው በጀት ዓመት ካስገባው አጠቃላይ 6 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ 2 ቢሊየን ዶላር የሚሆነው ገቢ በካርጎና ሎጂስቲክ አገልግሎት ያስገባው ነው። 

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡም የ2023 ምርጥ የካርጎና ሎጅስቲክስ ኦፕሬተርና የአፍሪካ ምርጡ የካርጎ ኦፕሬተር በሚል በሁለት ዘርፎች ለአምስተኛ ጊዜ መሸለሙ ይታወሳል። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም