የምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱና የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን--የኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት

ሆሳዕና፣ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱና የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ በኮሚሽኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተባባሪ አካላት ገለጹ።

ኮሚሽኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተባባሪ አካላት ያዘጋጀው ስልጠና በሆሳዕና ከተማ ተሰጥቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተጀመሩ ተግባራት ከግብ እንዲደርሱና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር የበኩላቸውን ለመዋጣት ዝግጁ ናቸው።

ከምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ቤተክህነት የመጡት መላከ ብስራተ ቀሲስ እንዳልካቸው ቦቸራ ለዘመናት የተገነባው የህዝቦች የአብሮነት ዕሴት እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እንደሃይማኖት አባት ዜጎች እርስ በርስ ያላቸው አንድነት፣ መቻቻል እና መከባበር እንዲጠናከር የማስተማር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ነው የገለጹት። 

በስልጤ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀጂ አብድረሂም አህመዲን በበኩላቸው፣ በእምነቱ አስተምህሮ መሰረት ለሰላምና አንድነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

በተለይም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ የጀመራቸው ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።   

እንደአገር ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ጠንካራ እሴት ቢኖረንም በአግባቡ ባለመያዛቸው ችግሮች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የማያግባቡን ነገሮችን ተቀራርቦ በግልጽ በመነጋገር መፍታት ይቻላል ያሉት ሀጂ አብድረሂም፣ የኮሚሽኑን ሥራ ከግብ እንዲደርስ ለዘላቂ ሰላምና አብሮነት ጠንክረው በመስራት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከከምባታ ጠምባሮ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ የመጡት አቶ ንጉሴ ፎዴ፣ በየትኛውም መንገድ የሚከሰቱ ችግሮችን ተወያይቶ መፍታት ባህል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በኮሚሽኑ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንዲሁም ልዩነትን ለማጥበብ የሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት ጠንክረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

 ከከምባታ ጠምባሮ ዞን ዶዮገና ከተማ የመጡት የሀገር ሽማግሌ አቶ ፍቅሬ ሱሊቶ በበኩላቸው  ለቀጣይ ትውልድ ጠንካራና የለማች ሀገር ለማስረከብ ሰላምን ማጠናከር ይገባናል፤ ለእዚህም የበኩሌን እወጣለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም የጀመራቸው ሥራዎች እንዲጠናከሩ ከኮሚሽኑ በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት አብሮነት ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። 

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተወጣጡ 574 ተባባሪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሆሳዕና ከተማ ሰጥቷል።

ተባባሪ አካላቱ በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ አካላትን ለመመልመል የሚያግዙ መሆኑም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም