አርቲስት አሊ ቢራ በተሰጠው መክሊት ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት ሲታገል የዘለቀ ታላቅ አርቲስት ነበር--ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
አርቲስት አሊ ቢራ በተሰጠው መክሊት ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት ሲታገል የዘለቀ ታላቅ አርቲስት ነበር--ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬደዋ፣ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ):-የክብር ዶክተር አርቲስት አሊ መሐመድ ሙሣ (አሊ ቢራ) ዕድሜውን በሙሉ ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት ሲታገል የነበረውን የጥበብ ገድሉንና በዘመኑ የፈጸማቸውን አኩሪ ሥራዎች ትውልዱ እንዲማርባቸው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
የክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ህይወት ያለፈበት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነስርዓት በተለያዩ ዝግጅቶች በድሬደዋ እየተከበረ ይገኛል።
በድሬደዋ ኢንተርናሽናል አየር መንገድ መግቢያ አካባቢ በተዘጋጀው የአርቲስቱ የቢልቦርድ ምርቃት የጀመረው የመታሰቢያ ዝግጅት ምሽቱን በጧፍ ማብራት ሥነስርአት ቀጥሏል።
በሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት፤ ድሬደዋ ካፈራቻቸው ድንቅና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ከሰሩ አርቲስቶች መካከል አርቲስት አሊ ቢራ ቀዳሚው ነበር።
ሁለገቡ አርቲስት ከግማሽ ዘመን በላይ ባዜማቸው ሙዚቃዎቹ ለሰው ልጅ እኩልነትና ነፃነት በሙሉ አቅሙ ሲታገልና ሲያታግል የነበረ ትውልድ የማይረሳው ድንቅ ሰው እንደነበር አስታውሰዋል።
"አሊ ቢራ ጭቆናንና ኢሰብአዊ ድርጊትን በአፅንኦት የሚጠየፍና ሰው በእኩልነት እንዲኖር የተጋ ድንቅ አርቲስት ነበር" ሲሉም ከንቲባው ገልጸዋል።
አርቲስት አሊ ቢራ በሁሉም ርዕሰጉዳዮች ላይ በተለያዩ የአገርና የውጭ አገር ቋንቋዎች ባቀነቀናቸው 300 የሚጠጉ ድንቅ ዘፈኖቹ አዲሱ ትውልድ ለቆመለት አንድ ዓላማና ግብ ሳይታክት እስከመጨረሻው ድረስ መታገል እንዳለበት ማስታማሩንም አውስተዋል።
አርቲስቱ በጥበብ ሥራዎቹ ያበረከታቸውን የጥበብ ውጤቶች ትውልዱ እንዲማርባቸው ለማስቻል የሚያግዙ ቋሚ መታሰቢያ ተቋማት በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ መቋቋማቸውን አድንቀው፣ አስተዳደሩም ተመሳሳይ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
"አሊ ቢራ ፈጣሪ በሰጠው ስጦታ ለሰው መስጠትን በተግባር ያሳየ የሰብአዊ መብት ታጋይ ነው" ያሉት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ በድሬዳዋ አስተዳደር ምክርቤት የመንግስት ቋሚ ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት ሰው በህይወት ዘመን ያለውን ሃብት፣ ዕውቀትና ጉልበት ለሰው ልጅ መስጠት አለበት።
"ያለንን ለሌለው መስጠት፣ መፋቀርና መተባበር የሚሰጠውን ታላቅ ደስታና የህሊና እረፍት ከአርቲስት አሊ ቢራ እንማራለን " ብለዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው፣ "ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ መስዋዕትነት በመክፈል ባቀጣጠለው የነፃነትና የእኩልነት ችቦ የአሁኑን ትውልድ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል" ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር አርቲስቱን ለመዘከር ያደረገውን ዝግጅት አድንቀው፣ የአርቲስቱን ሥራዎች ተሻጋሪና ቋሚ ለማድረግ በመጪው ህዳር 25 እንደ አገር የአሊ ቢራ ፋውንዴሽን ይጠናከራል ብለዋል።
"የድሬደዋ አስተዳደር አርቲስቱን በዚህ ታላቅ ዝግጅት በማስታወሱ የተሰማኝን ደስታና ስሜቴን መግለፅ ያቅተኛል" ያሉት ደግሞ የአርቲስት አሊ ቢራ ባለቤት ሊሊ ማርቆስ ናቸው።
በመታሰቢያ ሥነስርዓቱ ላይ ከአገርና ከውጭ አገራት የመጡ የአርቲስቱ ወዳጆችና ጓደኞች፣ አርቲስቶች እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በዛሬው ዕለትም አርቲስቱን ለመዘከር የድሬደዋ ከንቲባና አመራሮች እንዲሁም በርካታ ነዋሪዎች በተሳተፉበት የእግር ጉዞ ተካሂዷል።
የአርቲስት አሊ ቢራ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀጥል ታውቋል።