የስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ) ፦ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ከኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ጋር በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
በውይይታቸውም በክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የሙያ ደህንነትና ጤንነት ዙሪያ ከሚያደርጉዋቸው የጋራ ጥረቶች ባለፈ የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ እና የስታርትአፕ ስነ-ምህዳሩን በሚያሰፉ ተግባራት ላይ መምከራቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ ስርዓታችን ሀገራዊ ሀብት በመሆኑ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ ሆኖ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰናል ሲሉ ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪቱ እንዲሳለጥ ኢትዮ ቴሌኮም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ፍሬህይወት ታምሩና ማኔጅመንታቸው አረጋግጠውልናል ነው ያሉት፡፡
ለሀገራዊ ግቦቻችን ስኬት የጋራ ጥረትና ርብርብ አስፈላጊነቱን በመውሰድ ለሥራው ላሳዩት ፍፁም ቁርጠኝነት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋን እና ማኔጅመንታቸውን አመስግነዋል፡፡