በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች በጎንደር ከተማ ያስገነቧቸው የመማሪያ ክፍሎች ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች በጎንደር ከተማ ያስገነቧቸው የመማሪያ ክፍሎች ለአገልግሎት በቁ
ጎንደር ፤ ጥቅምት 26/2016 (ኢዜአ) ፦ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች በጎንደር ከተማ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነቧቸው የመማሪያ ክፍሎች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ውበት በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት የመማሪያ ክፍሎችን ያስገነቡት ኢንጂነር አክሱማዊት አብርሃና ጓደኞቻቸው ናቸው፡፡
የከተማው አስተዳደር፣ ወላጆች እና ትምህርት ቤቶቹ ለመማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የግንባታ ቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውም ገልጸዋል።
ቼቼላ እና ልዑል ዓለማየሁ በሚባሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተገነቡት የመማሪያ ክፍሎች ያለውን የክፍል ጥበት በማቃለል ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር ያግዛሉ ብለዋል።
ኢንጂነር አክሱማዊትና ጓደኞቻቸው ከዚህ በፊትም በከተማው በሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች 12 የመማሪያ ክፍሎችና አንድ ቤተ መጻህፍት አስገንብተው ለአገልግሎት ማብቃታቸውን አስታውሰዋል።
"በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች በከተማው የኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እያደረጉ ነው" ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ናቸው።
ከራስ አልፎ የሌሎችን ሕይወት በሚቀይሩ በጎ ተግባራት ላይ መሰማራት የትውልድ አሻራ ማስቀመጥ እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ከንቲባዋ፣ የከተማው አስተዳደር ኢንጂነር አክሱማዊትን ''የትምህርት አምባሳደር'' አድርጎ መሾሙን ተናግረዋል፡፡
ኢንጂነር አክሱማዊት በበኩላቸው ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ መገንባት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።
''በውጭ የምንኖር የከተማዋ ተወላጆች ያስተማረንን ህዝብና ሀገር መደገፍ ግዴታችን በመሆኑ ወደፊትም ለትምህርት ቤቶችን ደረጃ መሻሻል ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን'' ብለዋል።
በልዑል ዓለማየሁ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነቡት የመማሪያ ክፍሎች ከ2ሺህ በላይ ተማሪዎቹን ባልተጨናነቀ ሁኔታ ለማስተማር እንደሚያስችል የገለጹት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር እሸቴ አበራ ናቸው።
ባረጁ የመማሪያ ክፍሎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ስትማር ብትቆይም አሁን ላይ በአዲስ ተለውጠው በማየቷ መደሰቷን የገለፀችው ደግሞ የልዑል ዓለማየሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ምስራቅ ሲሳይ ናት።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ወላጆች፣ የትምህርት ቤቶቹ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል።