አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪን አነጋገሩ - ኢዜአ አማርኛ
አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪን አነጋገሩ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26 /2016(ኢዜአ):- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የተመድ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም አቶ ደመቀ መኮንን አስተባባሪ ጽህፈት ቤቱ ከመንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ያዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
አቶ ደመቀ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት፣ ህወሓትን ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ መደረጉ፣ የፌዴራል በጀትን ለክልሉ ማስቀጠልን ጨምሮ የተከናወኑ መሻሻሎችን አስረድተዋል ።
በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ የሽግግር ፍትሕ አሠራርን እና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ፤ በሂደት ላይ ያሉት ሥራዎችን በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
አስተባባሪው ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ በበኩላቸው የተባበሩት መንግታት ድርጅት አስተባባሪ ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብአዊ እና ልማት ጉዳዮች ላይ በአጋርነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አስተባባሪው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የተከናወኑ ሥራዎችን በተመለከተ መንግሥትን አድንቀዋል።
ዶክተር ራሚዝ ዋናው ፈተና ለሰብአዊ ሥራው የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖሩ መሆኑን አንስተው፤ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጥረታቸውን እንዲጨምሩ ለማድረግ ይሠራል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።