የህብረት ስራ ማህበራት ገበያ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው አንድ ላይ የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ማህበራት ገበያ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው አንድ ላይ የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ ነው
አዳማ፤ ጥቅምት 26/2016 (ኢዜአ)፡-የህብረት ስራ ማህበራት ገበያ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸውና የካፒታል አቅማቸው እንዲጎለብት እየተሰራ ባለው ሪፎርም ላይ መገናኛ ብዙሃን እንዲያግዙ የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ኮሚሽን ጠየቀ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ትግበራ ውስጥ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ሚናቸውን መወጣት የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዳማ ዛሬ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ በዚሁ ጊዜ በመላ ሀገሪቷ በርካታ የህብረት ስራ ማህበራት መኖራቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህ ማህበራት በብዛታቸው ልክ በሀገር ልማትና ዕድገት ላይ የሚጫወቱት ሚና ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
''ዘርፉ ሪፎርም ያስፈልገዋል'' ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በሪፎርሙም ካፒታል ከማሰባሰብ ባለፈ የተበታተኑትን የህብረት ስራ ማህበራት በዘርፍ በዘርፋቸው የማሰባሰብና የማዋሀድ ስራ እንደሚሰራ አንስተዋል።
ለአብነትም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ ሜካናይዜሽንና የእሁድ ገበያ የግብርና ምርት አቅርቦትና ገበያ ማረጋጋት የመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ ሪፎርም መሆኑን አመልክቷል።
በተጨማሪም በዘርፉ ውስጥ ያለውን የዘመናዊ አሰራርና አደረጃጀት፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማነቆዎችና ከኦዲትና ሀብት አስተዳደር ጋር ያላቸውን ውስብስብ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እንደሆነም ተናግረዋል።
ተቋማቱ በሰለጠነ የሰው ሃይል የሚመራ አማካሪ ቦርድ እንዲመሩ፣ ገለልተኛ የኦዲት ስርዓትና አሰራርና የህብረት ስራ ማህበራት ሊግ እንዲኖራቸው እንደሚደረግም አንስተዋል።
ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ባንክና የህብረት ስራ ማህበራት ፈንድ ኖሮም በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት የሚያስችል ሪፎርም መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ሪፎርሙን ለማሳካትም የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ህብረተሰቡ፣ ማህበራቱና መላው አባላቱ ስለ ሪፎርሙ በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ለማስቻል መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማህ ገብረስላሴ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ከ27 ሚሊዮን በላይ አባላትና ከ56 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ከ106ሺህ በላይ የህብረት ስራ ማህበራትና 402 ዩኒየኖች እንዳሉ አንስተዋል።
ሪፎርሙ ያስፈለገው የተበታተነ የካፒታል አቅማቸውን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ገበያውን መምራትና መወሰን እንዲችሉ ከእርሻ እስከ ምርት አቅርቦት፣ ግዥ፣ ማቀነባበሪያና እሴት ሰንሰለት ድረስ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የመድረኩ ዓላማም የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ህብረተሰቡንና አባላቱን በማንቃት ለንቅናቄው ስኬት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እንደሆነም አመልክተዋል።
በመድረኩ ከመንግሥትና ከግል የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።