ቀጥታ፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል - አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት በሁሉም መስክ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ገለጹ።

የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፤ የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ዘመናትን የተሻገረ ጥልቅ ወዳጅነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ጥብቅ ቁርኝት ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።

አገራቱ ሁለንተናዊ ትብብራቸውን በማጠናከር የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ይበልጥ አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በመደጋገፍ እየሰሩ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በውሃ፣ በመንገድ፣ በባቡር፣ በመብራት፣ በወደብ እና በሌሎች መስኮች የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርተው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በመተማመን ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የንግድና መሰረተ ልማት ትስስር ያላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የሁለቱ አገራት ህዝቦች በባህል፣ በቋንቋና ሌሎችም ማህበራዊ ትስስሮች ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን አምባሳደር ብርሃኑ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ምርት የሚጓጓዝበትን የመንገድ መሰረተ ልማት መፍትሄ ለማበጀት በቅርበት ንግግር መደረጉን አስታውሰው በጅቡቲ ጉምሩክ አገልግሎት የሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ እንዲያገኙም እየተሰራ ነው ብለዋል።

በወደብ የሚስተዋል የገቢ ዕቃ ክምችት በጊዜ እንዲነሳ የማድረግ ስራም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው የአፈር ማዳበሪያ እና መሰረታዊ ሸቀጦች በወቅቱ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት ጥገና በማከናወን የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲፈጠር ለማድረግ ከጅቡቲ መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለከፍተኛ ብልሽት የተጋለጠው የጋላፊ ከባድ ጭነት መተላለፊያ መንገድ ጥገና እንዲፋጠን ከአገሪቱ መንግስት ጋር ተከታታይነት ያለው ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ከጅቡቲ መንግስት ጋር በመተባበር ችግኞችን ከኢትዮጵያ በማስመጣት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ በባቡር፣ በወደብና የመሰረተ ልማት መስኮች ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ሲሆኑ የኢትዮ-ጅቡቲ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.አ.አ በ1984 እንደተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም