ቀጥታ፡

የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር ፒተር ፋሊያ የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 26 / 2016 (ኢዜአ)፦የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር ፒተር ፋሊያ የኢፌዴሪ አየር ኃይልን  መጎብኘታቸው ተገለጸ።

 በጉብኝቱ ወቅት የኢፌዴሪ አየር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ  እንዳሉት የኢትዮጵያ አየር ኃይል በግዳጅ አፈፃምና ተልዕኮን በብቃት በመወጣት ስኬታማ ከሆነው ና  ከአለም በአቭዬሽን ቴክኖሎጅ የላቀ ስም ካላቸው ሀገራት አንዷ ከሆነችው የቼክ ሪፐብሊክ ጋር ተቋማዊ ትስስሮችን ለማጠናከር የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኝት ትልቅ ፋይዳ አለው።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሪፎርሙ የአቭዬሽን ትጥቆችን ለማዘመን እያከናወነ ላለው ዘርፈ ብዙ ተግባራትም ተጨማሪ አቀም ይፈጥራል  ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከቼክ መንግስት ጋር በተለያዩ የአቭዬሽን ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ተባብሮ የመስራት የረዥም ጊዜ ልምድና መልካም ግንኙነት እንዳለው ያወሱት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በተለይም ከባለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የጀመሩትን የሰው ኃይል አቅም ስልጠና እና ሌሎች የሙያ መስኮችን ለማሥቀጠል ሁለቱ ሀገራት መስማማታቸውንም ገልፀዋል።


 

ጠቅላይ ሚንስትር ፒተር ፍያላ በበኩላቸው የቼክ  ሪፓብሊክ  የአቭዬሽን ሙያተኞች ከኢትዮጵያዊያን ጋር በአቭዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል ያከናወኑት የአውሮፕላኖች  እድሳት ዕድሜያቸውን የማራዘም አቅም አለው ብለዋል።

 በኢትዮጵያ አየር ኃይል የለውጥ ጉዞ የበረራ ትምህርት ቤት ሲሙሌተር (ምስለ በረራ)  የአፕግሬድ ስራዎችንም    አድንቀዋል።

ቼክ ሪፐብሊክ ና ኢትዮጵያ  ከ80 ዓመት በላይ የዘለቀ ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነት  አንዳላቸው ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም