በኒውዴልሂ በከባድ አየር ብክለት የተነሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ - ኢዜአ አማርኛ
በኒውዴልሂ በከባድ አየር ብክለት የተነሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 26/2016 (ኢዜአ)፡- በህንድ ዋና ከተማ ኒውዴልሂ በተከሰተው ከባድ የአየር መበከል ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ተገለጸ።
የህንድ ሜትሮሎጂ አገልግሎት በዋና ዋና ከተሞች የአየር መበከል እየጨመረ መምጣቱን ባስታወቀበት ሪፖርቱ በተለይም በኒውዴልሂ የሚታየው የአየር መበከል በከፍተኛ ደራጃ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።
የመዲናዋና አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች የአየር ብክለቱ ያመነጨው ብናኝና ጪስ በጤና ላይ ጉዳት እያስከተለ ስለ መሆኑ ቲአርቲ ዘግቧል።
ነዋሪዎቹ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ያስነበበው ቲአርቲ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መጠየቃቸውም ተጠቅሷል።
የአየር ብክለት መጠኑ እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ አስከፊ ሆኖ እንደሚቀጥል በመረጃው የተመላከተ ሲሆን በዜጎች ጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የሀገሪቱ መንግስት ገልጿል።
የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴርም ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኒውዴልሂ ከተማ የተከሰተው ከባድ የአየር መበከል የትምህርት ሂደቱን እንዳስተጓጎለው አመልክቷል።
በዚህም በከተማዋ የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እስከ ሳምንቱ መገባደጃ ድረስ ተዘግተው እንዲቆዩ መወሰኑን አስታውቋል።
ከተወሰኑ አመታት ወዲህ በኒውዴልሂ ከኢንዱሰትሪ ተቋማትና ሌሎች ተቋማት በሚወጡ ጪሶች ምክንያት የሚከሰተው የአየር ብክለት የከታማዋን ነዋሪዎች ሁለገብ እንቅስቃሴ እየገደበው እንደሚገኝ ተመልክቷል።