የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በአዲስ መልኩ ወደ ስራ መግባት ለአካታች የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻል ሚናው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በአዲስ መልኩ ወደ ስራ መግባት ለአካታች የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻል ሚናው የጎላ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በአዲስ መልኩ ወደ ስራ መግባት ለአካታች የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
በመርሃ ግብሩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መንግስት በሁሉም ዘርፎች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከልም በዚሁ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በጠባብና በማይመች ስፍራ አገልግሎት ይሰጥ አንደነበር አስታውሰው፤ የከተማ አስተዳደሩ አዲስ ቦታ በማዘጋጀት በአዲስ መልኩ እንዲደራጅ የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ከውጭ የሚገቡ አካል ድጋፍ ቁሳቁሶችን በራሱ አቅም ማምረት መጀመሩ ትልቅ እምርታ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለአካታች የጤና አገልግሎት ተደረሽነት መሻሻል ሚናው የጎላ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም ለማዕከሉ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ጥራቱን የጠበቀ የአካል ድጋፍና ታሃድሶ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም ብሔራዊ የአካል ድጋፍና ተሃድሶ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው፤ በተለያዩ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የተሃድሶ ማእከላትም ዳግም ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በዚህ ረገድ በጥቁር አንበሳ፣ ሐረር እና ጋምቤላ ሆስፒታሎች የነበሩ የተሃድሶ ማዕከላት ዳግም አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች መስኮች በአዲስ መልኩ ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
ይህም ተቋሙ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት ጠቁመዋል፡፡