የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በአዲስ ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ጥራት ያለው አገልግሎት በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በአዲስ ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ጥራት ያለው አገልግሎት በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በአዲስ ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ጥራት ያለው አገልግሎት በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በተበታተነ አግባብ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን ላይ በአዲስ መልኩ ተደራጅቶና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን በማካተት ለምረቃ በቅቷል፡፡
በዚህም ለአካል ጉዳት ድጋፍ የሚውሉ ምርቶችን በራሱ ከማምረት ባሻገር የታሃድሶ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ጊዜ ከሁለት ዓመት በፊት ተቋሙን መጎብኘታቸውን አስታውሰው፤ በወቅቱ በማይመች ቦታ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም አገልግሎቱን ይበልጥ ማዘመን በሚቻልበት አግባብ ተቋሙን እንደገና በአዲስ መልኩ ማደራጀት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ጥራት ያለው አገልግሎት በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
አሁን ላይ ተቋሙ ለመንቀሳቀስ የሚውሉ የአካል ድጋፍ መሳሪያዎችን በራሱ እንደሚያመርት ጠቁመው፤ በቀጣይ ሁሉንም አይነት አካል ጉዳቶችን ታሳቢ ያደረጉ አገልግሎቶችን ለመስጠት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ተቋሙ አቅሙን ከማጎልበት ባሻገር አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር ረገድም አበረታች ስራ መከናወኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጠናው አገራት የሚተርፍ አገልግሎት ለመስጠት መስራት እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ማዕከሉ በአዲስ እንዲደራጅ ድጋፍ ላደረጉ ወዳጅ አገራትንና ተቋማትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጥር ወር 2013 ዓ.ም ተቋሙ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ይሰጥ በነበረበት ስፍራ በመገኘት አጠቃላይ እንቅስቃሴውን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡