ቀጥታ፡

የመንገድ መሰረተ ልማቶች ተገቢው ጥበቃና ቁጥጥር ስለማይደረግላቸው በአጭር ጊዜ ለብልሽት እየተዳረጉ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 25/2016 (ኢዜአ)፦የመንገድ መሰረተ ልማቶች ተገቢው ጥበቃና ቁጥጥር ስለማይደረግላቸው በአጭር ጊዜ ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ።

የመንገዶችን ደህንነት ለመጠበቅ የጭነት ተሽከርካሪዎችን የክብደት መጠን ከመቆጣጠር ጀምሮ ሌሎችም ጥብቅ የቁጥጥር ስራዎች መጀመራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አሰተዳደር የክብደት መጠን መቆጣጠሪያ ሚዛን ጣቢያዎችን በማቋቋም የቁጥጥር ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።

የቁጥጥር ስራ ከሚከናወንባቸው ጣቢያዎች መካከል ኢዜአ የሻሸመኔ የክብደትና መጠን መቆጣጠሪያ ሚዛን ጣቢያ የስራ ክንውንን ተመልክቷል።

በጣቢያውም የተሽከርካሪዎችን የጭነት ልክ በማረጋገጥ ህግ ተላልፈው የሚገኙት ተጠያቂ እየተደረጉ መሆኑን የጣቢያው ሃላፊ አቶ ወንዱ ደምሴ ገልጸዋል።


 

የመቆጣጠሪያ ጣቢያው የ24 ሰአት አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ጠቅሰው የመንገድ ደህንነትን የማስጠበቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንገድ ደህንነትን የመጠበቅ ስራ የተለያዩ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው ለጋራ ደህንነትና ሃብትን ለመጠበቅ የሁላችንም ጥረት ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።

በከፍተኛ በጀት በተለያዩ የሀገሪቷ አቅጣጫዎች የሚገነባውን የመንገድ መሰረተ ልማት በመጠበቅ ለረጅም ጊዜ አገልገሎት እንዲሰጥ በማድረግ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ነው ያሉት።

የምእራብ አርሲ ዞን ትራንስፖርት ቢሮ ተቆጣጣሪ ከዱ ቱሉቦጊ፤ መንገዶች የሁሉ ነገር መሰረትና የሀገር ሃብት በመሆናቸው በጋራ መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል።


 

የተሽከርካሪ ባለንብረቶችም ጊዜያዊ ጥቅምን ለማግኘት እነዚህን መሰረተ ልማቶች ከሚያበላሽ ተግባር በመቆጠብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የሻሸመኔ መንገድ ኔትወርክ የመንገድ ደህንነት ቡድን መሪ ሙሉቀን አበራ፤ ከፍተኛ ወጭ የወጣባቸው መንገዶች በአጠቃቀም ችግር በአጭር ጊዜ ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ለመንገዶች ደህንነት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ስለሚገባ ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጣቢያው ያገኘናቸው አሽከርካሪዎችም መሰል ጣቢያዎች በተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

በጭነት ጉዳይ አንዳንድ ባለንብረቶች የማስገደድ ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው ይህም ለስራቸው እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንገድ ድህንነት መጠበቅ ማለት የራስን ህይወት፣ የሰዎችን ህይወትና የሃገረን ንብረት ከጉዳት መጠበቅ በመሆኑ የሁላችንም ትኩረት ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

መንግሥት መጠነ ሰፊ የሆነ የመንገድ አውታር ግንባታና የማስፋፋት ስራ፣ ደረጃ የማሳደግ እና የጥገና ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም