ቀጥታ፡

ከቡና ምርት ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ  ከምርምር ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው 

ዲላ ፤ ጥቅምት 25/ 2016(ኢዜአ)፡-  የቡና ምርትን  ጥራት በመጠበቅ  ከዘርፉ  ገቢ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከምርምር ተቋማትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሰልጣን ገለጸ።


ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ጋር በመተባበር የቡና ምርትና ግብይት ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መሐመድ ሸምሱ በወቅቱ እንዳሉት፤  ቡና ከምርት እስከ ግብይት ዓለም አቀፍ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ዝግጅት ይፈልጋል።

ቡናን በጥራት አዘጋጅቶ  በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የምርምር ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።

የዘርፉ ምርታማነትን በማሳደግና ቴክኖሎጂ በማፍለቅ እንዲሁም ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ አሰራር ለመከተል ቅንጅታዊ ጥረት እየተደረገ  መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም  የቡና ምርት ጥራት ተጠብቆ አቅርቦቱን በማሻሻል ከዘርፉ ገቢ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከምርምር ተቋማትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

በተያዘው የበጀት ዓመት ከ350 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ  መታቀዱንም ጠቅሰዋል።

በተለይ ቡናችንን ከማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ በጥራትና በልዩ ጣዕም ቡና አቅርቦት ላይ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመዋል። 


 

ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቡና በተፈጥሮ ጣዕሙ ያገኘውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚመጥን የገቢ አቅም ለማሳደግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገለጹት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ናቸው።

በተለይ የበይነ መረብ ትምህርት በመክፈት ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ እውቅትንና ልምድን ከማሰባሰብ ባለፈ የቡና ምርምርና ጥናት ማዕከል የማቋቋም ስራ በተቋሙ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በቡና ምርትና ግብይት ያሉ ችግሮችን በማቃለል  የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትስስር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሁሴን አንቦ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ቡና  በተፈጥሮ ጣዕሙ የተለየ በመሆኑ በዓለም ላይ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም  ምርትና ግብይቱ የእውቀት ክፍተት ያለበት በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ከምርምር ተቋማት ጋር በትስስር መስራቱ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር በቀጣይ አብረው ለመስራት የሚያስችል የጋራ የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው በቡና ልማት ያከናወናቸው ተግባራት የተመለከተ  የመስክ ምልከታም ተካሄዷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም