ቀጥታ፡

በቢሾፍቱ ከተማ በተከናወነው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወንዶች አንዱዓለም በላይ በሴቶች ፍቅርተ ወረታ አሸነፉ

ቢሾፍቱ ፤ጥቅምት 25/2016 (ኢዜአ)፦ በቢሾፍቱ ከተማ ዛሬ በተከናወነው 10ኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በወንዶች አንዱዓለም በላይ ከፌዴራል ፖሊስ በሴቶች ፍቅርተ ወረታ ከመቻል አሸነፉ።
በውድድሩ በወንዶች አንዱዓለም በላይ ከፌዴራል ፖሊስ 1ኛ፣ ሰቦቃ ንጉሥ  ከኦሮሚያ ክልል 2ኛ እንዲሁም ክብሮም ደስታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3ተኛ በመሆኑ ጨርሰዋል።
በሴቶች በተደረገው ውድድር ፍቅርተ ወረታ ከመቻል 1ኛ፣ ጋዲሴ ሙሉ ከኦሮሚያ ፖሊስ 2ኛ እንዲሁም የኔነሽ ጥላሁን ከኦሮሚያ ክልል 3ኛ ሆነው በመጨረስ አሸናፊ ሆነዋል።


 

በውድድሩ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁት አትሌቶች 40ሺህ ብር ፣ ዋንጫና ሜዳሊያ ለእያንዳንዳቸው ተበርክቶላቸዋል።
በቬተራን ወድድር በወንዶች ገዛኸኝ ገብሬ 1ኛ ፣ ጋፌ አባይ 2ኛ እንዲሁም አብደላ ሱሌማን 3ኛ  ደረጃን በመያዝ ሲያጠናቅቁ ፤በሴቶች አበሩ ዘውዴ 1ኛ፣ አይሻ ኑሪ 2ኛ እንዲሁም አዳነች ተስፋዬ 3ኛ ደረጃን በመያዝ  አጠናቀዋል።
በወንዶች ፌዴራል ፖሊስ  እንዲሁም በሴቶች ኦሮሚያ ፖሊስ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ችለዋል።
በውድድሩ ላይ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና አቃቤ ንዋይ አቶ ተፈራ ሞላ ተገኝተዋል።
በውድድሩ ላይ 322 ወንዶች እና 108 ሴቶች በድምሩ 430 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
በአዋቂዎችና ወጣቶች 30 ኪሎ ሜትር ፤በወንዶች ከ50 ዓመት በላይና በታች እንዲሁም በሴቶች ከ50 ዓመት በታች በተመሳሳይ 15 ኪሎ ሜትር ውድድሮች ተከናውነዋል። 
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ላሸንፉ አትሌቶች አጠቃላይ ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ ሽልማት ተበርክቷል።
የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ በቋሚነት ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም