ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ንጣፍ ሥራ በቅርቡ ለማስጀመር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 25/2016 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መመዘኛ መስፈርትን ተከትሎ እድሳት እየተደረገለት ያለው የአዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ንጣፍ ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጨዋታዎችን በብቸኝነት ሲያስተናግድ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በካፍና ፊፋ የተቀመጠውን መመዘኛ ባለማሟላቱ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ መታገዱ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎ ስታዲየሙን ወደ ሥራ ለማስገባት በሰኔ 2013 ዓ.ም ጨረታ ወጥቶ የመጀመሪያው ምዕራፍ እድሳት ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን ለእድሳቱ በመንግሥት በኩል 150 ሚሊየን ብር መመደቡን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የተመልካች መቀመጫ፤ የተመልካች መታጠቢያ ቤቶች፤ የተጨዋቾች መልበሻ ክፍልና ተመልካችና ሜዳውን የሚለየው አጥር በእድሳት ሥራው ከተጠናቀቁት ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የደኅንነት ካሜራዎች፤ ስክሪኖች፣ የቪአይፒ ወንበሮች ደግሞ እየተሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን የአዲስ አበባ ስታዲየም የሲቪል ምህንድስና ሥራ ቢጠናቀቅም የሳር ንጣፍ ሥራው እስከ አሁን አለመጀመሩን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ በሲቪል ምህንድስናው ብቃታቸው የተረጋገጠ ተቋማትና ባለሙያዎች ቢኖሩም ከሳር ንጣፍ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፈቃድ ያገኘ ድርጅት እንደሌለ አመልክተዋል።

የሳር ንጣፉን የሚያከናውን ደረጃውን የሚያሟላ ድርጅት አለመኖሩ የስታዲየሙን የእድሳት ሥራ እንዲጓተት ማድረጉንና ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባው ጠቁመዋል። 

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው ለሳር ንጣፍ ሥራ የሚያግዙ ብዙ ተግባራት ቀድመው የተከናወኑ ቢሆንም ንጣፉ እስከ አሁን አለመጀመሩን ገልጸዋል።


 

በዚህም ጉዳይ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

የንጣፍ ሥራውን ከፈረንሳይና ከቱርክ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ባለሙያዎችን አምጥቶ ሥራውን ለማከናወን የዋጋ ጉዳይ ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝና በቅርቡ ሥምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የስታዲየሙን እድሳት ሥራ በፍጥነት ለመጨረስ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ስታዲየሙ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መመዘኛ መስፈርትን መሰረት በማድረግ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እድሳት እየተደረገለት እንደሚገኝ ነው አምባሳደር መስፍን ያብራሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም