በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 25/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ማለፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታ፤ የሕብረተሰቡ የቁጠባ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልና ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ ይናገራሉ።
በመሆኑም ባንኮችን ጨምሮ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ የቁጠባ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 19 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል።
የቁጠባ መጠኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ25 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ተናግረዋል።
ሁሉን አቀፍ የቁጠባ ስርዓት ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ሴቶችና አነስተኛና መካከለኛ የሕብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ ሌሎችም የቁጠባ ልምድ እንዲያዳብሩ ተደርጓል ብለዋል የባንኩ ምክትል ገዥ።
የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓትን በተለያዩ አማራጮች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የቁጠባና የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ተደርጓልም ነው ያሉት።
የዲጂታል ስርዓቱ መስፋፋት፣ የአዳዲስ ባንኮች ወደ ስራ መግባት፣ የካፒታል ገበያና የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የመግባት እድል ተዳምረው ለቁጠባ ማደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑም አብራርተዋል።
የፋይናንስ ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም መስኮች የዲጅታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በ2025 ዓ.ም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።