ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የጂቡቲ ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነት የሁለትን ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትያረጋገጠ ነው - ዶክተር ዓለሙ ስሜ 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያና የጂቡቲ ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነት የሁለቱን ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትያረጋገጠ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ተናገሩ።  

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ከጅቡቲ የመሰረተ ልማትና ኢኪዩፕመንት ሚኒስትር ሃሰን ሁመድ ኢብራሂም ጋር ውይይት አካሂደዋል።   

ውይይቱም የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፣ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬና ሌሎች የሁለቱም አገራት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። 

በውይይቱም የአገራቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና ወዳጅነት የትብብር መስኮች ተነስተዋል። 

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ዘመናትን የተሻገረ ጥልቅ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።

የሁለቱን አገራት ዜጎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግም በመሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች  ዘርፎች ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን አረጋግጠዋል።


 

የጅቡቲ የመሰረተ ልማትና ኢኪዩፕመንት ሚኒስትር ሃሰን ሁመድ ኢብራሂም በበኩላቸው የኢትዮጵያና ጅቡቲ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። 

በቀጣይም የሁለቱን አገራት የወደብና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ትብብር በማስፋት የአገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም