ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ብቃት ያለው ዜጋ እንዲያፈሩ ልምምድ ልውውጥ ላይ ትኩረት ይደረጋል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፡-የኮተቤ የትምህርት ዩንቨርሲቲ ተገቢውን እውቀትና ክህሎት የጨበጠ  ዜጋ ለማፍራት እያደረገ ያለውን ውጤታማ ተግባራት ወደ ሌሎች የትምህርት ተቋማት ለማስፋት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ገለፀ።

የኮተቤ የትምህርት ዩንቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎቹ የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።


 

ዩኒቨርሲቲው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሳይንስ ሼርድ ካምፓሱ 12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ካስቀመጣቸው 75 ተማሪዎች መካከል 72ቱ የማለፊያ ነጥብ ማምጣታቸውን ገልፀዋል።

በሽልማት መርኃ ግብሩ የተገኙት የመዲናዋ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር  ዩንቨርሲቲው ብቃት ያለው የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል። 

ይህንንም ተሞክሮ በመዲናዋ በሚገኙ በሌሎች ትምህርት ቤቶች ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። 

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው፤ ዩንቨርሲቲው  በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮች ለመቀነስ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።


 

በተለይም ብቁ መምህራንንና የትምህርት ባለሙያዎችን በማፍራት ተማሪዎችን በቂ እውቀት እንዲጨብጡ ለማድረግ  ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አገር የሚያደግው በተማረ የሰው ኃይል መሆኑን ጠቁመው ተማሪዎችን ከታችኛው የክፍል እርከን ጀምሮ በእውቀትና ክህሎት ማነጽ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።  

በአገር አቀፍ ፈተናው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎችም በዛሬው እለት የታብሌትና የሰርተፍኬት ሽልማት እንደተበረከተላቸው ገልጸዋል። 

ዩኒቨርስቲው በቀጣይም ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን በማፍራት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። 

በሳይንስ ሼርድ ካምፓሱ በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ተማሪዎች   መካከል ኖላዊ ጌትዬና ራሄል ገረመው 600 በላይ ነጥብ ካመጡ ተማሪዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። 


 

ተማሪዎቹ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገባቸው ከራሳቸው ጥረት በተጨማሪም የመምህራኖቻቸውና የቤተሰቦቻቸው ድጋፍ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ነው የሚናገሩት።


 

በቀጣይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን እውቀት በመቅሰም ቤተሰቦቻቸውንም ብሎም አገራቸውን በቅንነት  ለማገልገል ተስፋ መሰነቃቸውን አመልክተዋል።

በሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የሚማሩ ተማሪዎች እዚህ ደረጃ እንደደርሱ ከፍተኛ እገዛ ሲያደርጉ ለነበሩ መምህራንም በዩንቨርሲቲው የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመርኃ ግብሩ የዩንቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም