የድሬዳዋ ስታዲየምን ሜዳ ሰው ሰራሽ የሣር ንጣፍ የማልበስ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ስታዲየምን ሜዳ ሰው ሰራሽ የሣር ንጣፍ የማልበስ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው
ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 24/2016(ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ ስታዲየምን ሜዳ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ ሰው ሰራሽ የሣር ንጣፍ የማልበስ ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለፀ።
የድሬዳዋ ስታዲየምን ሜዳ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ የሰው ሰራሽ የሳር ንጣፍ የማልበስ ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለፀ።
የድሬዳዋ ስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የአስተዳደሩ የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት የስታዲየሙን ሜዳ በሰው ሰራሽ ሣር የማልበስ ስራን ዛሬ ተመልክተዋል።
ኮሚሽነር ፊራኦል ቡልቻ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት በ50 ሚሊዮን ብር እየተከናወነ ያለው ሜዳውን በሣር ንጣፍ የማልበስ ሥራ በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቋል።
የሜዳውን ደረጃ እና እየተሰሩ ያሉ ተግባራት በቅርብ ቀናት ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በሚመጡ ከፍተኛ አመራር ተገምግሞ ዕውቅና እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።
በድሬዳዋ በዘርፉ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በየትምህርት ቤቱ በፓይለት ደረጃ ለተመሠረቱና የድሬዳዋን ዝና ይመልሳሉ ተብለው ለሚጠበቁ ታዳጊ ክለቦች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ያግዛል ብለዋል።
የድሬዳዋ ስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት፤ የመጫወቻ ሜዳው በሰው ሰራሽ የሣር ንጣፍ እንዲለብስ መደረጉ አገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጨዋታዎችን ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ ለማስተናግድ የሚያስችል ነው።
"አርቴፊሻል ሣር የማልበስ ሥራው 90 በመቶ የተጠናቀቀ በመሆኑ ሜዳው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድሮችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል" ሲሉም ገልጸዋል።
ከንቲባ ከድር እንዳሉት ድሬደዋ በአገር አቀፍ ደረጃ በስፖርት ዘርፍ የነበራትን ገናና ስም ለመመለስ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
በከተማዋ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት በስፋት እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ላለፉት 50 ዓመታት ያገለገለውን የድሬዳዋ ስታዲየም በዘመናዊ መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጉን ተናግረዋል።
ስታዲየሙ አገራዊና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲካሄዱበት ለማስቻል ሰው ሰራሽ የሣር ንጣፍ የማልበሱ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
"እነዚህ ሥራዎች ስፖርተኞችንና በፕሮጀክት የታቀፉ አዳጊ ወጣቶችን የሚያነቃቁና ድሬዳዋ ቀደም ሲል የነበራትን ከፍታ ለመመለስ ያግዛሉ" ብለዋል።
ድሬዳዋ በስፖርት ዘርፍ በተለይም በእግር ኳስ ዘርፍ ለአገራችን ጭምር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ገናና ስፖርተኞች መፍለቂያ እንደነበረች ያስታወሱት ደግሞ የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት የድሬዳዋ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት የአስተዳደሩ አመራሮች ህብረተሰቡን ከጎናቸው በማሰለፍ በስፖርቱ ዘርፍ እያደረጉት ያለው ድጋፍ በቀጣይ የድሬዳዋን ዝና በላቀ ደረጃ ለመመለስ የሚያስችል ነው።
በኢንተርናሽናል ሜዳው የሣር ማንጠፉ ሥራው እየተጠናቀቀ በመሆኑ ሁለተኛው ዙር ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮችን ያስተናግዳል ብለዋል።