በ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር 430 አትሌቶች ይሳተፋሉ - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር 430 አትሌቶች ይሳተፋሉ - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፦በቢሾፍቱ ከተማ ነገ በሚካሄደው 10ኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር 430 አትሌቶች እንደሚወዳደሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ ውድድሩን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የፌዴሬሽኑ የውድድርና ተሳትፎ ባለሙያ አቶ አሸብር ደምሴ ውድድሩ ለአትሌቶች የውድድር እድል ከመፍጠር ባሻገር ተተኪዎችን ለማፍራት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከናወኑ የጎዳና ላይ ውድድሮች አቋማቸውን ለመፈተሽ እንደሚያግዛቸውም ጠቅሰዋል።
በውድድሩ ላይ 322 ወንዶች እና 108 ሴቶች በድምሩ 430 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።
በአዋቂዎችና ወጣቶች 30 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በወንዶች ከ50 ዓመት በላይና በታች እንዲሁም በሴቶች ከ50 ዓመት በታች በተመሳሳይ 15 ኪሎ ሜትር ውድድር እንደሚካሄድም ነው አቶ አሸብር የገለጹት።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ40 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚበረክትላቸውና በአጠቃላይ ከ300 ሺህ ብር በላይ ለሽልማት መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ በቋሚነት ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል አንዱ ነው።
ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው ዘጠነኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በወንዶች አትሌት ፋንታሁን ሁነኛው፤ በሴቶች አትሌት አፀደ ባይሳ ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
በወንዶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴቶች ኦሮሚያ ፖሊስ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ መሆናቸውም አይዘነጋም።