ቀጥታ፡

መከላከያ ሠራዊት በወገኖቹ የተካደበትን ቀን ሁሌም እንዳይደገም እንዘክረዋለን

 አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት24 / 2016 (ኢዜአ)"ሠራዊቱ በወገኖቹ የተካደበትን ቀን ሁሌም እንዳይደገም እንዘክረዋለን" ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ሰሜን ዕዝ  በወገኖቹ የተካደበት 3ኛ ዓመት የመታሰቢያ መርሃ-ግብር "እንዳይደገም ሁሌም እንዘክረዋለን" በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ድንበር እየጠበቀ ፣የአርሶ አደሩን ሰብል እየሰበሰበ፣ የአንበጣ መንጋን እያባረረ ና  የኮቪድ ወረርሽኝን በመከላከል አሰተዋጽኦ አበርክቶ በድካም ላይ  ጋደም ባለበት በወገኖቹ ተክዶ ጥቃት የተፈፀመበት  ድርጊት  በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ጠባሳ የተመዘገበበት ቀን መሆኑን  የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ  አስታውሰዋል።

ለግል ስልጣንና ጥቅም  ሲባል ዘርና ወገን ለይቶ  የራስን ጠባቂ እና ጋሻ  መከላከያ ሠራዊትን በጭካኔ በመጨፍጨፍ ሀገርን ያለጠባቂ ለማስቀረትና መንግስትን ለመጣል የተደረገው  ሙከራ በአለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅና ኢትዮጵያን ለመከራ ጥሎ ያለፈ ቀን መሆኑን ተናግረዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ በትግራይ ክልል ትሞህርት ቤቶችን እየገነባ ፣አቅም የሌላቸው ተማሪዎች እያስተማረ ፣ የጤና ኬላ እየሠራ እና መሠረተ ልማቶችን እያስፋፋ   መቆየቱንም  አስረድተዋል።


 

ህዝቡ ከሠራዊቱ ጋር ተዛምዶ ተዋልዶና ቤተሰብ ሆኖ በኖረበት ክልል በፀንፈኛ ፖለቲከኞች ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት  መፈፀሙን ያነሱት ፊልድ ማርሻሉ ይህን ክፉ ድርጊት   እንዳይደገም ሁሌም ይዘከራል ብለዋል።

ጦርነቱ በሁሉም ወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ከዚህ ታሪክ መላው ኢትዮጵያዊ ተምሮ እንዳይደገም በመዘከር  ህዝቡ ለሠላም መሥራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኬንያ ባለሙሉ ስልጣን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ  በእለቱ የተካሄደውን የፓናል ዉይይት መድረክ በመሩበት ወቅት እንዳሉት ጥቅምት 24   በተፈጠረው ነገር ከልባችን ተፀፅተን ለሠላም በህብረት ልንሰራ  ይገባል ብለዋል።

ሰራዊቱ የተካደበት  3ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ጄኔራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ መኮንኖች ፣የሠራዊት አባላትና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም