ወጣቶች የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረቅ፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለአገር ግንባታ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረቅ፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለአገር ግንባታ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፦ ወጣቶች የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረቅ፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለአገር ግንባታ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አሳሰበ።
የሰላም ሚኒስቴር "በጎነትን ለአብሮነት" በሚል መሪ ኃሳብ ለስምንተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 693 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዛሬ በጅማ ዩኒቨርስቲ አስመርቋል።
የወጣቶችን አመለካከት፣ ክህሎትና ሞራል በማሳደግ የአገርን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በተጀመረው ብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር በጅማና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ 2 ሺህ 856 ወጣቶች በዛሬው እለት ተመርቀዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ለበጎነት ስራ የሚያስፈልገው የትምህርት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰብን ለማገልገል የውስጥ መሻትን ማሳየት ነው።
ወጣቶች የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት ግንባታ ለማጽናት ትርክቶችን ማረቅ እንዲሁም ልዩነቶችን በአንድነት ጥላ ሥር መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ አርበኝነት ያሉ ትርክቶች በአገር ግንባታና ሉዓላዊነት ላይ የጎላ አበርክቶ ነበራቸው ብለዋል።
"ትርክት አገር ይገነባል፣ አገር ያፈርሳል" በኢትዮጵያም ትርክት አዎንታዊና አሉታዊ ሚና እንደነበረው አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ልዩነትን በመጨፍለቅ አንድነትን ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረቅ፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለአገር ግንባታ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በእያንዳንዱ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ የሚደረግ ተሳትፎ በአገር ግንባታ ላይ መሰረት መጣል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በአገር ግንባታ ላይ መሳተፍ ትልቁ የህይወታችን መርህ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ታፍራና ተከብራ ትኖር ዘንድ ወጣቶች በአገረ መንግሥት ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ሁላችንንም በሰላም የምታኖር፣ የተመቸችና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የዜጎች ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ልዩነት የሚፈታው በሰላማዊ ውይይት፤ ስልጣን የሚያዘው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ነው ያሉት አቶ ብናልፍ፣ ፍላጎትን በኃይል ለማሟላት የሚደረግ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ዋጋ እንዳስከፈላት ገልጸዋል።
ወጣቶች ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሰማሩባቸው አካባቢዎች የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረምና የሰለጠነ የፖለቲካ አውድ እንዲፈጠር በማድረግ በአገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ፤ ኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ተምሳሌት እንድትሆን ወጣቶቹ አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ለበጎነት ራስን መስጠት ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ በስልጠናቸው ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለፅዳትና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት አውለዋል ነው ያሉት።
ወጣቶቹ የተረፋቸውን ሳይሆን ካላቸው ቀንሰው በመስጠት ለሀገራቸው እድገት ያላቸውን ቀናኢነት በተግባር ማሳየታቸውንም እንዲሁ።