ቀጥታ፡

ከሰሞኑ የተከሰቱት ጉንፋንና መሰል ወረርሽኞች እንዳይዛመቱ ኅብረተሰቡ አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን የጉንፋንና መሰል ወረርሽኞች እንዳይዛመቱ ኅብረተሰቡ አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት የጤና ባለሙያዎች አሳሳቡ።

የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ በ2 ሺህ ናሙናዎች ላይ ባደረገው ምርመራም የጉንፋንና መሰል ወረርሽኞች  መከሰታቸውን ማረጋገጡ ይታወሳል። 
 

በአዲስ አበባ የዚሁ ወረርሽኝ ምልክት የተገኘባቸውና ሕክምና እየተከታተሉ ያሉ ግለሰቦች ወይዘሮ ትእግስት ዘውዱ  እና ሚኪያስ ጥበቡ ምልክቶች ከተለመደው የጉንፋን ዓይነት ይለያል ብለዋል።
 

ሕመሙ ሲጀምር ማስነጠስ፣ ራስ ምታት፣ በሰውነት መገጣጠሚያዎች አካባቢ የቁርጥማት ስሜት ከማስከተሉም በተጨማሪ ምራቅን መዋጥ እስከሚያዳግት ድረስ የጉሮሮ ሕመምና ሳል እንዳለው ገልጸዋል። 

ይህንን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ ኅብረተሰቡ የተከሰተውን ጉንፋንና  መሰል ወረርሽኝ እጅ በመታጠብ፣ አፍና አፍንጫን በመሸፈን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል  ተናግረዋል።

በየካ አባዶ ጤና ጣቢያ ጠቅላላ ኃኪም ዶክተር መቅደላዊት ዓለሙ በበኩላቸው በጤና ጣቢያው የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው ወደ ጤና ተቋሙ የሚመጡ ታካሚዎቸ ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ያስረዳሉ።

ለሕሙማኑ ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው ኅብረተሰቡ አስፋለጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምከረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።  

በአዲሱ ገበያ ጤና ጣቢያ የጤና ባለሙያ የሆነችው ሲስተር ቤዛዊት በፍቃዱ ከሰሞኑን የተከሰተው ጉንፋን መሰል ህመም ለመታከም የሚመጡ ህሙማን ከፍተኛ የራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለትና ማስነጠስ እንዲሁም ሳል ይታይባቸዋል ብለዋል።  

ኅብረተሰቡ መሰል የበሽታው መልክት ሲታይባቸው ወደ ጤና ተቋም አስቀድሞ በመሄድ በሽታው ወደ ሌላ እንዳይዛመት ማድረግ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።  

የየካአባዶ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ከድር የሱፍ ደግሞ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ለበሽታው ተጋላጭነትን መቀነስና ጤናን መጠበቀ ይገባል ነው ያሉት።      


 

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በቂ እረፍት በመውሰድ፣ ፈሳሽና ትኩስ ነገሮች በመጠቀምና ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል። 

በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ዶክተር መብራቱ ማሴቦ በበኩላቸው፤ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡዋቸውን ምክረ-ሃሳቦችን በመተግበርና በርና መስኮቶቻችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖራቸው በማድረግ መከላከል እንደሚቻልም ገልጸዋል። 


 

ህሙማኑ ስርጭቱ እንዳይስፋፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በቂ እረፍት በመውሰድ፣ ፈሳሽና ትኩስ ነገሮች በመጠቀም፤ በሽታውም ከባሰባቸው ተገቢውን ህክምና መወሰድ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም