ቀጥታ፡

አገር አቋራጭ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች በጉዞ ሂደት ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፦ በአገር አቋራጭ ጭነት ወቅት በኢትዮ-ጅቡቲ የጉዞ ሂደት የሚያጋጥሙ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመንገድ ላይ ችግሮች መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አገር አቋራጭ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች ጠየቁ።   

በኢትዮ-ጅቡቲ ጉዞ ወቅት የከባድ ጭነት አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገልጸዋል።  

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በጅቡቲ ፊካዶስ-12 የኢትዮጵያ አገር አቋራጭ ጭነት ተርሚናል  ከ50 የነዳጅ ቦቴ እና 100 በላይ የደረቅ ጭነት አሽከርካሪዎች ጋር ተወያይቷል።  

በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ፣ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፣የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፣የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎን  ጨምሮ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።  

በውይይቱ ላይ አገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች በጭነት አገልግሎት ወቅት በኢትዮ-ጅቡቲ የጉዞ ሂደት የሚያጋጥሙ የወደብ አገልግሎትና የመንገድ ላይ ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ከመንገድ ብልሽት፣ ከጸጥታና ደህንነት፣ ከወደብ አገልግሎት አሰጣጥና ክፍያ እንዲሁም ከጉዞ ሂደት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች አንስተዋል።

በዚሁ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ  በችግር ውስጥ ሆናችሁ አገራችሁን እና ሕዝባችሁን በማገልገል ላይ በመሆናችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።  


 

የአገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች የሥራ ባህሪ የማይመች ሞቃታማ የአየር ጸባይን፣ ምቾት የጎደለው መንገድን እንዲሁም የጸጥታና ደህንነት ችግሮችን ተቋቁሞ መስራትን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።

አገር አቋራጭ የጭነት አሽከርካሪዎች ከነዚህ ችግሮች ባለፈ ለረጅም ጊዜ ከቤተሰብ ተለይተው ለአገር ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በችግር ውስጥ ሆነው  ወገናቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ በመሆናቸው በጉዞ ወቅት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንገድ ላይ እያጋጠማቸው የሚገኘውን ችግር ለመፍታትም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጅቡቲ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በመምከር መፍትሔ እንዲያገኙ ትኩረት  መሰጠቱን ገልጸዋል።

በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፥ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት አሽከርካሪዎች እያጋጠሟቸው የሚገኙ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም