የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የኮተቤ የትምህርት ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ሽልማት ተበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የኮተቤ የትምህርት ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ሽልማት ተበረከተ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፦ የኮተቤ የትምህርት ዩንቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎች ሽልማት አበረከተ።
ዩኒቨርሲቲው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሳይንስ ሼርድ ካምፓሱ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ካስቀመጣቸው 75 ተማሪዎች መካከል 72ቱ የማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል።
ይህንንም ምክንያት በማድረግ የማለፊያ ውጤት ላስመዘገቡ የካምፓሱ ተማሪዎች የታብሌትና የሰርተፊኬት ሽልማት አበርክቷል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በዚሁ ጊዜ፤ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ ብቁ እውቀትን የተላበሰ ዜጋ ማፍራት የግድ ይላል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት እንደ አገር የሚታየውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ ሁሉም የዘርፉ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት በትኩረት መሥራት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ በአገር አቀፉ የ2015 ዓም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ላይ ያስመዘገቡትን አኩሪ ውጤት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡም ሊደግሙት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር፤ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየውን የተማሪዎች የውጤት ማሽቆልቆል ችግር ለማቃለል በልዩ ትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የሳይንስ ሼርድ ካምፓሱ ብቁና የተማረ ትውልድን ለማፍራት እያከናወናቸው ያለው ተግባራት የሚበረታታ በመሆኑ ልምዱን ለሌሎች እንዲያካፍልም ጥሪ አቅርበዋል።
ተማሪዎቹም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቆይታቸው በቂ እውቀት በመጨበጥ የማኅበረሰቡን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ተግባራት ላይ መስራት እንደሚገባቸው ነው ያነሱት።
በመርኃ-ግብሩ ላይ የዩንቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ከ845 ሺህ በላይ ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ነጥብ ያስመዘገቡት 27 ሺህ 267 ተማሪዎች ናቸው።