የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ አስመረቀ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀይል መቆራረጥን የሚቀርፍ የራሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ /ሰብስቴሽን/ አስመርቋል።
በሁለት ዓመት ከግማሽ ገደማ ጊዜ የወሰደው የኃይል ማሰራጫ ግንባታ 40 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸከም አቅም ያለው ሲሆን ሁለት ትራንስፎርመሮችም አሉት ተብሏል።
ለግንባታው 9 ሚሊየን ዶላር ወጪ መደረጉም ተገልጿል።
በምረቃ መርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ አባላት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላን ጨምሮ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም የራሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ አልነበረውም።
ይህም የኃይል መቆራረጥ ሲያጋጥመው በሥራ ላይ እንቅፋት ይፈጥር እንደነበር አስታውሰው ዛሬ የተመረቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫም ይህንን ችግር ያስቀራል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቱ አየር መንገዱ ደረጃውን የጠበቀ የደንበኞች አገልግሎት ለመስጠትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።