ቀጥታ፡

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ከጅቡቲ የመሰረተ ልማትና ኢኪዩፕመንት ሚኒስትር  ጋር ተወያዩ

 አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2016 (ኢዜአ)፦  የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ከጅቡቲ የመሰረተ ልማትና ኢኪዩፕመንት ሚኒስትር ሃሰን ሁመድ ኢብራሂም ጋር ውይይት አካሄዱ።  

በውይይቱም የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፣ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬና ሌሎች የሁለቱም አገራት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። 

በውይይቱም የአገራቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና ወዳጅነት የትብብር መስኮች ተነስተዋል። 


 

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ዘመናትን የተሻገረ ጥልቅ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የሁለቱን አገራት ዜጎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግም በመሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች  ዘርፎች ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን አረጋግጠዋል።

የጅቡቲ የመሰረተ ልማትና ኢኪዩፕመንት ሚኒስትር ሃሰን ሁመድ ኢብራሂም በበኩላቸው የኢትዮጵያና ጅቡቲ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። 

በቀጣይም የሁለቱን አገራት የወደብና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ትብብር በማስፋት የአገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም