ቀጥታ፡

ወቅትን ብቻ ተከትሎ የሚገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ዓመቱን ሙሉ እንዲገባ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 23/2016(ኢዜአ)፡- ወቅትን ብቻ ተከትሎ የሚገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ዓመቱን ሙሉ የመደበኛውን የወጪና የገቢ የሎጀስቲክ አገልግሎት ሳያስተጓጉል እንዲገባ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል ።

በግብርና እና የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የሚመራ ዐቢይና ቴክኒካል ኮሚቴ  የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የምክክር መድረክ አካሂዷል። 

መድረኩን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ እንዳሉት ምክክሩ ከመደበኛ ወጪና ገቢ የሎጀስቲክስ አገልግሎት ጎን ለጎን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን ለማሳለጥ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል። 

የልዑካን ቡድኑም በአፈር ማዳበሪያ ግዥና ስርጭት ወቅት ያጋጥሙ የነበሩ ክፍተቶችን በማሻሻል ለ2016/17 ዓ.ም በጀት ዓመት የምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል። 

በአፈር ማዳበሪያ ግዥና ስርጭት አሰራር ላይ መንግስት ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ የአሰራር ሂደቱን የሚመራና የሚከታተል ቦርድ ተዋቅሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ከዚህ በፊት የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ወቅቱን ባለመጠበቁ የመደበኛ ሎጀስቲክስ አገልግሎቱን ሲጎዳ ቆይቷል ፤ በተያዘው ምርት ዘመን መሰል ጫና እንዳይከሰት አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል። 

በተለይ ወቅትን ብቻ ተከትሎ የሚገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ዓመቱን ሙሉ የመደበኛውን የሎጀስቲክ አገልግሎት ሳያስተጓጉል እንዲገባ ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት መደረሱን ተናግረዋል።  

በተጨማሪም ከፌደራል እስከ ወረዳ ከሚገኙ የኢትዮጵያና የጅቡቲ መንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም የገቢና ወጪ ምርቶችን የማጓጓዝ ሂደት እና የአፈር ማዳበሪያን ወደ አገር ቤት የማስገባት ስራ ጎን ለጎን እንዲሰራ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ በዘንድሮው የ2016/17 በጀት ዓመት የምርት ዘመን ከሚገዛው 23 ሚሊየን ኩንታል ውስጥ 13 ሚሊየኑ ተገዝቶ የማጓጓዝ ስራ እንደተጀመረ ገልጸዋል። 

የመጀመሪያዋ የአፈር ማዳበሪያ ጫኝ መርከብ ጀቡቲ ወደብ ደርሳ ወደ አገር ቤት የማጓጓዝ ስራ እንደተጀመረ ተናግረዋል። 

በዘንድሮው የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በተሻለ ሁኔታ በማሳለጥ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ በግብርና እና የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የሚመራ ዐቢይና ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

በዘንድሮው ዓመት ግዥ የሚፈጸምበት የአፈር ማዳበሪያ ባለፈው ዓመት ግዥ ከተፈጸመበት 13 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ውስጥ የ9 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው አስታውሰዋል። 

ይህን በመጠንና ጥራት ብዛት ያለው የአፈር ማዳበሪያም መኪና እና የባቡር ትራንስፖርት በመጠቀም በገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት ሳያስከትል እንዲገባ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መሪነት ጅቡቲ የሚገኙ የባቡር፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስና የመርከብ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችም በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር  ብርሃኑ ጸጋዬ፥ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ወጪና ገቢ ምርቶችን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ማሳለጥ የሚያስችል የጋራ ዕቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በጅቡቲ የሚገኙ የኢትዮጵያ ተቋማትም የአገርን ወጪና ገቢ ምርት ማሳለጥ የሚያስችል ቅንጅታዊ አሰራር መፈጠሩ ስራውን በውጤት ለመምራት ያስችላል ብለዋል። 

ኢምባሲውም ከጅቡቲ መንግስትና በጅቡቲ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ተቋማት ጋር በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል። 

በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሣ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሮ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፣ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በውይይቱም ለ2016/17 ዓ.ም በጀት ዓመት የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያ በቀን ከ20 ሺህ ቶን በላይ በጅቡቲ ወደብ ከመርከብ ላይ እየተራገፈ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በትናንትናው ዕለት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በጅቡቲ ኦልድ ፖርት (ኤስ.ዲ.ቲቪ ወደብ) ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን በይፋ ማብሰራቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም