የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድን የተከተለና የአገራትን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድን የተከተለና የአገራትን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 23/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድን የተከተለና የማንንም አገር ጥቅምና መብት የማይነካ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም መብትና የያዘችውን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ በማስመልከት ኢዜአ አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና እና የህዝብ ተወካችዮች ምክር ቤት አባልና ዓለም አቀፍ የህግ ምሁር ሳዲቅ አደምን አነጋግሯል።
አምባሳደር ጥሩነህ፤ በማብራሪያቸው የባህር በር የመጠቀም መብት የኢትዮጵያውያን የረጅም ጊዜ ጥያቄ መሆኑን ያነሳሉ።
የቆየውን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ የሰጥቶ መቀበል መርህንና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ጥረት ዘመኑን የዋጀና የአገራትን መብት የማይነካ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የተከተለችው የዲፕሎማሲ አካሄድ የባህር በር ካላቸው አገራት ጋር በድርድርና በስምምነት የመጠቀምና በጋራ የመልማት መርህ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድን የተከተለና የማንንም አገር ጥቅምና መብት የማይነካ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የባህር በር የመጠቀም መብት ጥያቄው በጀመረችው አካሄድና በሰላማዊ አማራጮች መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ አካሄድን መከተል ቀጣናዊ ትስስርን መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ የኢትዮጵያም አካሄድ በዚሁ መልኩ መቀጠል አንዳለበት አምባሳደር ጥሩነህ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አገራት ጋር በትብብርና በሰጥቶ መቀበል መርህ በመሥራት የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የምጣኔ ኃብት እድገት ለማሳለጥ የያዘችውን አቋም አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታልም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል የባህር በር መኖር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ይህ እውን እንዲሆን በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና ዓለም አቀፍ የህግ ምሁሩ ሳዲቅ አደም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባህር በርን አስመልክተው ያነሷቸው ሃሳቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከውሃ እና ከባህር በር ጋር ተደንግገው ያሉ ህጎችን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄም ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ሊደግፉ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ህጎች ተደንግገው ያሉ መሆናቸውንም አንስተው በእነዚህ ድንጋጌዎች ተጠቅመውም በርካታ አገራት የባህር በር ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ስለዚህም ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው ሃሳቦች በዓለም አቀፍ ህጎች ተቀባይነት ያላቸው፣ በሌሎች ተሞክረው ውጤት ያስገኙ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ያቀረበችው አማራጮች ኢትዮጵያ በጋራ ለመልማት ትልቅ ሥፍራ የምትሰጥ መሆኑን ያመላከተ ነው ሲሉ አቶ ሳዲቅ አደም ተናግረዋል፡
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1982 በጀማይካ የተፈረመው የዓለም የባህር ሕግ ስምምነት የባህር በር የሌላቸው አገራት ወደብ ካለበት ቦታ የመድረስና የመመለስ እንዲሁም በባህር ውስጥ የሚገኙ ኃብቶችን ጭምር መጠቀምን የሚፈቅድ ነው።
በዓለም ላይ የባሕር በር የሌላቸው 44 አገራት፤ በዓለም ላይ ካለው ሕዝብ 40 በመቶ እንደሚሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።