የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው የሠላም ግንባታ ሥራ መስራት ይገባል- ዶክተር ስዩም መስፍን - ኢዜአ አማርኛ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው የሠላም ግንባታ ሥራ መስራት ይገባል- ዶክተር ስዩም መስፍን
አሶሳ፤ ጥቅምት 23/2016 (ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘውን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ቀጣይነት ያለው የሠላም ግንባታ ሥራ መስራት እንደሚገባ የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን ተናገሩ።
የክልሉን ሠላም ማጠናከር ዓላማ ያደረገ የዘላቂ ሰላም ፕሮጀክት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ይፋ ተደርጓል።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ስዩም መስፍን በዚህ ወቅት በክልሉ በተለይ የመተከልን ሠላም ለመመለስ የተከናወኑ ሥራዎችን አድንቀዋል።
"ዘላቂ ሰላም ቀጣይነት ያለው የሠላም ግንባታ ሥራ ይጠይቃል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በቀጣይም የክልሉን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የአጭርና የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ነድፎ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህ ሂደት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠልና የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የተጀመሩ የሰላም ግንባታ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የዘላቂ ሰላም ፕሮጀክት የክልሉን ሠላም ከማጠናከር ባለፈ ለተጎዱ ተቋማት መልሶ ግንባታ ትኩረት እንደሚያደርግ ዶክተር ስዩም ተናግረዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገውን ፕሮጀክት ጨምሮ በክልሉ ለዘላቂ ሰላም ለሚከናወኑ ሥራዎች ሚኒስቴሩ ባለሙያ በመመደብ ጭምር ድጋፉን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮችን በመጋፈጥ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ልማት ስኬት ለማምጣት የሚያስችል መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።
"በክልሉ የህብረተሰቡን ህይወት ማሻሻል የሚቻለው አሁን የተገኘው ሰላም ተጠናክሮ ሲቀጥል ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለዚህም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለሦስት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው የዘላቂ ሰላም ፕሮጀክት በተለይ የመተከል ዞንን የግጭት ምክንያቶች ለመለየት የሚያስችል ጥናት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የአቅም ግንባታ፣ የእርቀ ሠላምና የማህበረሰብ ውይይቶችን ማከናወን የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት መሆኑ ተመልክቷል።
ፕሮጀክቱን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀ መርኃ-ግበር ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ዶክተር ተመስገን ዲሳሳን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮች፣ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።