የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የቻይና ኤምባሲ ነጻ የትምህርት ዕድል ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የቻይና ኤምባሲ ነጻ የትምህርት ዕድል ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 23/2016 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች በቻይና ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በተገኙበት ተፈርሟል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የቻይና ኤምባሲ ለዩኒቨርሲቲው ተመሳሳይ ዕድሎችን ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅድመ-ምረቃና በድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን በማሰልጠን የጥናትና ምርምር ፕሮጀክቶችን በመደገፍና ሌሎችም ዘርፎች የቻይና መንግስት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያወጣ ገልጸዋል።
በዚህም የቻይና መንግስት በማህበራዊ ልማትና በትምህርት ላይ ድጋፍ በማድረግ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ወሳኝ የልማት አጋር መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም የተፈረመው ይህ ነጻ የትምህርት ዕድል በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችና መምህራንን ለማሰልጠን ዕድል የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝ አስተዳደርነት በሚያደርገው ጉዞ ብቁ መምህራንና ተማሪዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በበኩላቸው፤ የቻይና ኤምባሲ ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ዩኒቨርሲቲውን በተለያዩ መስኮች ሲደገፍ የቆየ መሆኑን አንስተዋል።
ቻይና የኢትዮጵያ ወሳኝ የልማት አጋር መሆኗ በሁሉም ዘርፍ የሚገለጽ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዩኒቨርሲቲዎች የሰለጠነ የሰው ኃይል ማምረት ላይም ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።