ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር የመጠቀም ጥያቄ በቀጣናው አገራት የጋራ ተጠቃሚነትና እድገትን የሚያሳልጥ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 23/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር የመጠቀም ጥያቄ በቀጣናው አገራት የጋራ ተጠቃሚነትና እድገትን የሚያሳልጥ መሆኑ ተገለጸ።

እኤአ በ1982 በጀማይካ በተፈረመው የዓለም የባሕር ሕግ ስምምነት መሠረት የባሕር በር የሌላቸው አገራት ወደብ የመጠቀም እንዲሁም በባሕር ውስጥ የሚገኙ ኃብቶችን የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። 

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ ከመሆኑ በተጨማሪ በጋራ መልማትንና ቀጣናዊ ትስስርን ያለመ መሆኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያን የባህር በር የመጠቀም ጥያቄ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም ይህንኑ መሰረት ያደረገና የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ሶሬሳ ደምሴ፤ የባህር በር የሌላቸው አገራት ወደብ የመጠቀምና በጋራ የመልማት መብት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያም የባሕር በር የመጠቀም ጥያቄ በቀጣናው አገራት የጋራ ተጠቃሚነትና እድገትን የሚያሳልጥ መሆኑን ጠቅሰው በጋራ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ ውይይቶችንና ስምምነቶችን ለማድረግ ያሉትን እድሎች መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ በሰጡት ማብራሪያ መሰረት በሰጥቶ የመቀበል መርሕ በጋራ መልማትና መጠቀም ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል።

የቀጣናው ሀገራትን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር የዲፕሎማሲ አካሔድ መከተለም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምሕርና ተመራማራ ሰለሞን ተፈራ፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቀጣናውን አገራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና አብሮ የማድግ እድሎች የሚያሰፋ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የሌሎች አገራትን ብሔራዊ ጥቅም የማይጋፋ፣ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ላይ ተመርኩዞ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር የመጠቀም መሰረታዊ ጥያቄ የቀጣናው አገራት በቅንነት ወስደው በጋራ ለመልማትና ለመጠቀም በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የባሕር በር ዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ የጋራ ተጠቃሚነትንና አብሮ መልማትን መሠረት ያደረገ ሲሆን የመንግስታቱ ድርጅት እኤአ በ1952 ባሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 390/5 መሠረትም የባሕር በር ጥያቄ  አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጠው ነው።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም