ቀጥታ፡

ለ2016/17  የምርት ዘመን በቀን ከ20 ሺህ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ከመርከብ ላይ እየተራገፈ  ነው

 አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23/2016 (ኢዜአ)፡- ለ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን በቀን ከ20 ሺህ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ በጅቡቲ ወደብ ከመርከብ ላይ እየተራገፈ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።

የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን የሚከታተል ኮሚቴ የ2015/16 በጀት ዓመት የነበሩ በጥንካሬና ድክመት የተነሱ ጉዳዮችን በመገምገም ለ2016/17 የምርት ዘመን የቅድመ ዝግጅትና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ፣ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ጨምሮ የግብርና፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጅቡቲ መንግሥት ተወካዮች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲራጅ አብዱላሂ፥ የ2016/17 በጀት ዓመት የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት ያሉ ጠንካራና መፍትሔ የሚሹ አፈፃጸሞችን አቅርበዋል። 

ይህንን ተከትሎ አሁን ላይ በቀን ከ20 ሺህ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ከመርከብ ላይ እየተራገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራን በስኬት ለማከናወን የባለድርሻ ተቋማትን ያካተተ ኮሚቴ በማቋምም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሂደቱም የመንገድ ብልሽት፣ የማሸጊያ ከረጢት አለመጣጣም፣ የተሽከርካሪ እጥረትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ወደብ ላይ የደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ለማንሳት በክፍተት የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ለዚህም የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን በመጠቀም ወደብ የደረሰን የአፈር ማዳበሪያ በሚፈለገው ፍጥነት ወደ አገር ቤት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። 

ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ለማቅረብ እየተሠራ ነው ተብሏል። 

በትናንትናው ዕለት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በጅቡቲ ኦልድ ፖርት (ኤስ.ዲ.ቲቪ ወደብ) ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን በይፋ ማብሰራቸው የሚታወስ ነው። 

በግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ልዑካን ቡድን የ2016/17 ዓ.ም የግብርና ምርት በጀት ዓመት የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት ላይ ምልከታ በማድረግ በጥንካሬና በክፍተት የሚስተዋሉ ጉዳዮች ላይ የቀጣይ አቅጣጫ ማመላከት የሚያስችል ጉብኝትና ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም