የዘንድሮው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት በከፍተኛ ዝግጅትና ቅንጅት የሚከናወን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት በከፍተኛ ዝግጅትና ቅንጅት የሚከናወን ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 23/2016 (ኢዜአ)፦ የዘንድሮው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት ያለምንም መስተጓጎል በከፍተኛ ዝግጅትና ቅንጅት የሚከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፤ በትናንትናው እለት በጅቡቲ ኦልድ ፖርት (ኤስ.ዲ.ቲቪ ወደብ) በመገኘት የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት ማብሰራቸው ይታወቃል።
የማዳበሪያ ማጓጓዝ ሂደቱ በይፋ መጀመሩን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ የዘንድሮው የማጓጓዝ ሂደት ከፍተኛ ዝግጅትና ቅንጅት የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።
በ2015/16 የነበረው የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት በመዘግየቱ በአርሶ አደሩ የአቅርቦት ፍላጎት ላይ መስተጓጎል መፍጠሩን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ለተያዘው የ2016/17 በጀት ዓመት የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የማጓጓዝ ስራ ከወዲሁ መጀመሩ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅት ወቅቱን የጠበቀ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እንዲኖር የማጓጓዝ ስራ ጀምሯል ብለዋል።
የዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት ከባለፈው ዓመት መስተጓጎል በመማር በከፍተኛ ዝግጅትና ቅንጅት የሚከናወን መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራውን በተሳለጠ መንገድ ለማከናወን ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከምድር ባቡር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያውን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ለማቅረብ በተቀናጀ መልኩ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፤ እንደ ሀገር የግብርና ምርታማነት ዕድገት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ለዚህም የግብርና ግብዓት አቅርቦት ትልቁን ድርሻ መያዙን ጠቅሰው በመንግስት በኩል ለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለተኛ እና መካከለኛ ዘመን የአስር ዓመት የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ የግብርና ምርታማነትን በእጥፍ የማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ በሎጀስቲክስ አቅርቦት በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በዘንድሮው ዓመትም የአፈር ማዳበሪያን በተሳለጠና በተቀላጠፈ መንገድ ለማጓጓዝ በሎጀስቲክስ ዘርፍ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተመራው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በጅቡቲ እያደረጉት በሚገኘው ቆይታም በአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝና በወደብ የሎጀስቲክስ እንቅስቃሴ ላይ ከጅቡቲ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛል።