በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው 

 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 23/2016 (ኢዜአ) ፡- በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

በስብሰባው የምክርቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመክፈቻ ንግግራቸው የምክክሩ ትኩረትን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 በመድርኩ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ዘላቂ የራስ አቅም መፍትሔዎችን በያዘ ፍኖተ ካርታ ላይ እና በወቅታዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

ምክር ቤቱ የቀጣይ አራት ወራት ዋና ዋና የአደጋ ምላሽ ሥራዎች ላይ መክሮ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 ከማለዳው ጀምሮ "ሰብዓዊ ድጋፍ፣ ገመና እና ሉዓላዊነት፣ ፈተናዎችና መውጫ መንገዶች" በሚል የተዘጋጀ ሰነድ ለምክርቤቱ በመቅረብ ላይ ነው።


 

የመንግስት ኮሙዪኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትላንት በሰጡት መግለጫ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በአደጋ ስጋትና በአደጋዎች ዙሪያ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተሰጡ ምላሾች ላይ ምክክር እንደሚያደርግ መናገራቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የሰብአዊ እርዳታ የማቅረብ አቅሟንና ችግሩን ለመፍታት ያሉ እድሎችና አማራጮች ላይ ምክር ቤቱ እንደሚወያይና የአደጋ ስጋት መከላከልና መቆጣጠርን አስመልክቶ የሚቀርቡለትን ሪፖርቶች በመገምገም ቀጣይ የስራ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ መግለጻቸውም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም