ኮሪያ ሪፐብሊክ በመድኃኒት አቅርቦት ለኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኮሪያ ሪፐብሊክ በመድኃኒት አቅርቦት ለኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- ኮሪያ ሪፐብሊክ በመድኃኒት አቅርቦት በተለይም በመድኃኒት አቅርቦት እሴት ሰንሰለት ለኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የሀገሪቱ የፓርላማ አባላት አስታወቁ።
ከኮሪያ ሪፐብሊክ የመጡ የፓርላማ አባላት የልኡክ ቡድን የኢትዮጵያን መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጎብኝተዋል።
የፓርላማ አባላቱ አገልግሎቱ እያከናወነው ስለሚገኘው ተግባር በአገልግሉቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን በተቋሙ ውስጥ የሚገኘውን የመድኃኒት ማከማቻም ጎብኝተዋል።
የልኡክ ቡድኑ መሪና የኮሪያ ሪፐብሊክ የፓርላማ አባል ዩን ሆጁንግ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በመድኃኒት አቅርቦት እሴት ሰንሰለት ዘርፍ አበረታች ስራ እየሰራች ትገኛለች።
በተለይ በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ የመድኃኒት ማከማቻዎች ሀገሪቱ በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖራት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በዚህም የኮሪያ ሪፐብሊክ በዘርፉ ይበልጥ ከኢትዮጵያ ጋር የምትተባበርበትንና ከዚህ ቀደም ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ ለማጠናከር የሚያስችል ሁኔታ መመልከታቸውን ነው የፓርላማ አባሉ ያብራሩት።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በመድኃኒት አቅርቦት ዘርፍ እየተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት ለፓርላማ አባላቱ ማብራሪያ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ በተለይ በዓለም አቀፉ የመድኃኒት ፈንድ በኩል ለኢትዮጵያ በርካታ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን ጠቅሰው በዓለም አቀፍ ተቋሙ በኩል ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የፓርላማ አባላቱ መናገራቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም፤ የመድኃኒት አቅርቦት እሴት ሰንሰለቱ ዲጂታላይዝ እንዲሆን በቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ዶክተር አብዱልቃድር ገልጸዋል።