ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና  የኮሪያ ሪፖብሊክ ፓርላማዎች የትብብር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ይሰራሉ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ እና የኮሪያ  ሪፖብሊክ ፓርላማዎች የትብብር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚሰሩ መሆኑ ተገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ  ከኮሪያ ሪፖብሊክ የፓርላማ ልዑካን ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፖብሊክ 60 አመት የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸውና ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።

የኮሪያ ሪፖብሊክ ፓርላማ ልዑካን ቡድን አባላት የኢትዮጵያ ጉብኝትም ይህንኑ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።

ከልኡካን ቡድኑ ጋር ውይይት ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ ሁለቱ አገራት ያላቸው ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነት በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአገራቱ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ትብብር መኖሩን አንስተው ከእነዚህ መካከል በጤናው ዘርፍ ያለው አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ልዑካኑ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ኮሪያ ሪፖብሊክ  በዘርፉ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታጠናክር ጠይቀዋል።

የሁለቱ አገራት ምክርቤቶች በልምድ ልውውጥና አብሮ በመስራት ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለባቸውም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ የኢትዮ ኮርያ ፓርላሜንታዊ ወዳጅነት አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የኮርያ አቻውም ግንኙነታቸው እንዲጠናከር የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኮሪያ ሪፖብሊክ ፓርላማ ልዑካን ቡድን መሪ ዶክተር ቼልሶ አን፤ ልዑኩ  ኮሪያ ሪፖብሊክ ለኢትዮጵያ ድጋፍ የምታደርግባቸውን ዘርፎች ለመለየት ጉብኝት ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በማደግ ላይ ላሉ አገራት ሪፖብሊክ ኮሪያ ድጋፍ የማይለይ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም