ቀጥታ፡

የግብርና ምርት እድገትን ለማስቀጠል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ሥርዓቱ እንዲሻሻል ተደርጓል 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡-  የግብርና ምርት እድገትን ለማስቀጠል የአፈር ማዳበሪያ ግዥና የአስተዳደር ሥርዓቱ እንዲሻሻል መደረጉን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ። 

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በጅቡቲ ኦልድ ፖርት (ኤስ.ዲ.ቲቪ ወደብ) ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን በይፋ አብስረዋል። 

በማብሰሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሣ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፣ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለስልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ፣  በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ጨምሮ የግብር ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 


 

በማብሰሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፤ ለ2016/2017 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

የወጭ ንግድ አቅምን የሚያሳድጉ እንደ ስንዴ፣ አቦካዶ፣ ቡናና ሻይ ያሉ ምርቶችን በስፋት ማምረት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። 

በግብርና ምርታማነት ላይ እየተመዘገበ ያለው ተጨባጭ ውጤትም የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች የግብዓት አይነቶች ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል። 

የግብርና ምርታማነት እድገትን ለማስቀጠል የአፈር ማዳበሪያ ግዥና አስተዳደር ሥርዓቱ እንዲሻሻል በማድረግ ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ የመጀመሪያ ዙር የማጓጓዝ አካል የሆነው የአፈር ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጅቡቲ ወደብ ደርሳ ወደ አገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራ በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ቀደም ብሎ መፈጸሙም ማዳበሪያን በወቅቱ ለማድረስ፣ የማጓጓዝ ስራ ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጠር ማድረጉን  ተናግረዋል። 

የአፈር ማዳበሪያ በማጓጓዝ ሂደቱ ሃይ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ለሚገኙት የግብርና ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ለጅቡቲ ህዝብና መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ፍላጎትን ለመሙላት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

ለ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመጠን፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በመፈጸም የማጓጓዝ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል። 

በባለፈው የ2015/16 በጀት አመት ከ13 ሚሊየን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን አስታውሰው በዘንድሮው የ2016/17 የምርት ዘመንም ከ23 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ይፈጸማል ብለዋል። 

የአፈር ማዳበሪያው በጊዜ ማስገባት መቻሉም ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች፣ ለበጋና መኸር ወቅት ሰብል ልማት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫዎት ተናግረዋል። 

የአፈር ማዳበሪያ ስርጭቱን በፍትሕዊነት ለማካሄድ የቅድመዝግጅት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። 


 

የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለስልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ፤ የኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራ በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለእኛ ጭምር የሚተርፉ በመሆናቸው በሚቀጥሉት ወራትም የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራው በማሳለጥ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም