በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ ወርቅ አዘዋዋሪዎችን በመከታተል ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ ወርቅ አዘዋዋሪዎችን በመከታተል ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 22 / 2016(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ የወርቅ ዝውውር በሚያደርጉ አምራቾችና ነጋዴዎች ላይ ክትትል በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
የክልሉ የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት የማዕድን ልማት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአኝዋሃ ዞን ዲማ ወረዳ በመድረክና በመስክ ተካሄዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ፤ በክልሉ ዲማ፣ አበቦ፣ ጋምቤላና መንጌሽ ወረዳዎች ወርቅ በስፋት እንደሚመረት ገልጸዋል።
ሆኖም በኮንትሮባንድ ችግር ምክንያት ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ አይደለም ብለዋል።
የግብይትና የማምረቻ ፈቃድ ወስደው የወርቅ ምርት በመሰወር የኮንትሮባንድ ንግድ በሚያካሄዱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እየሰፋ ሊመጣ የቻለው የወርቅ ግብይትና የማምረቻ ፈቃድ ያላቸው ሳይቀሩ በህገ ወጥ የወርቅ ዝውውሩ በመሳተፍቸውና በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ የላላ በመሆኑ ነው ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላ ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ የተቋቋመው የፀረ-ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል በህገ ወጦች ላይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል ብለዋል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ አኳታ ቻም በበኩላቸው፤በዘርፉ እየተበራከተ የመጣውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ለሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
መስሪያ ቤታቸው ህጋዊ ሆነው ለሚያመርቱና በግብይት ዘርፍ ለተሰማሩ ድጋፍ ለመሰጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢያቸው ከሚወጣው የወርቅ ምርት አኳያ ወደ ብሔራዊ እየገባ ያለው ዝቅተኛ መሆኑን ከግምገማው መድረከ መገንዘባቸውን የተናገሩት ደግሞ በዲማ ወረደ የጆሩ ቀበሌ የፀረ-ኮንትሮባንድ አባል አቶ ኦፔዮ ዲድሙ ናቸው ።
በአካባቢያቸው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት ጠንክረው በመስራት የድርሻውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት የሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ለሁለት ቀናት በመድረክና በመስክ ምልከታ ተገምግሟል።