በፋይናንስ ተቋማት እስከ 100 ሺህ ብር ተቀማጭ ያለው ግለሰብ የመድን ሽፋን ያገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በፋይናንስ ተቋማት እስከ 100 ሺህ ብር ተቀማጭ ያለው ግለሰብ የመድን ሽፋን ያገኛል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- በፋይናንስ ተቋማት እስከ 100 ሺህ ብር ተቀማጭ ያለው ማንኛውም ግለሰብ የመድን ሽፋን እንደሚያገኝ የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዛሬ በይፋ ስራ መጀመሩን አስመልክቶ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ እና የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ደስታ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ፈንዱ በንግድ ባንኮችም ሆነ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለሚቆጥበው ወይም ለሚያስቀምጠው ማህበረሰብ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን በባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ የመውደቅ አደጋ ቢያጋጥም አስቀማጮች ካሳ የሚያገኙበት ስርዓት ነው።
በኢትዮጵያ ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገት የአገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት ጤናማ፣ ለአደጋ ያልተጋለጠና የተረጋጋ በማድረግ ለማጠናከርና የገንዘብ አስቀማጮች ጥበቃ እና ለፋይናንስ ሥርዓት ለማረጋጋት ሲባል ፈንዱ መቋቋሙ ተብራርቷል።
በተጨማሪም የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድን እንደ አንድ ተጨማሪ የሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ማረጋጊያ ለማድረግ መሆኑም በደንቡ ተመላክቷል።
ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በስተቀር ከሕዝብ ተቀማጭ እንዲሰበስቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጣቸው የፋይናንስ ተቋማት በሙሉ የፈንዱ አባል የመሆን ግዴታ ያለባቸው መሆኑን እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ፤ ከዛሬ በኋላ በእያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ ያለው የእያንዳንዱ አስቀማጭ ተቀማጭ ገንዘብ እስከ 100 ሺህ ብር ያለው ገንዘብ በመድን የተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በባንኮች ገንዘብ ከሚያስቀምጡት አብዛኛዎቹ ወይም 95 በመቶ የሚሆኑት በባንክ ያለው የገንዘብ መጠን ከ100,000 ብር በታች መሆኑን ተናግረዋል።
የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸው ያስቀመጡት ገንዘብ፣ የፌደራል መንግስት ወይም የመንግስታዊ ድርጅቶች ተቀማጭ ገንዘብ፣ የፋይናንስ ተቋም የውጭ ኦዲተሮች ተቀማጭ ገንዘብ፣ በፋይናንስ ተቋም ተደማጭነት ያለው (ከ2 በመቶ በላይ የአክሲዮን ባለቤት) ባለአክሲዮን የተያዘ ተቀማጭ ገንዘብ በመድን ሽፋን ውስጥ አይካተቱም ብለዋል።
የፋይናንስ ተቋማት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የዋና ስራ አስፈጻሚ፣ የከፍተኛ ስራ አስፈጻሚና ከነሱ ጋር የመጀመሪያ የስጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦችም ተቀማጭ ገንዘብ በመድን ሽፋን አይካተቱም።
ወደፊት ፈቃድ የሚውስዱ ባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ መሰብሰብ ከመጀመራቸው በፊት የፈንዱ አባል መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የፈንዱ አባል የሆኑት የፋይናንስ ተቋማት በየዓመቱ ከያዙት ወይም ካላቸው አማካይ ተቀማጭ ገንዘብ 0 ነጥብ 3 በመቶ ለፈንዱ መክፈል እንዳለባቸውም ነው አቶ መርጋ ያስረዱት።
በመድን ፈንዱ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሰበብሰቡና በበጀት ዓመቱ 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን አብራርተዋል።
ከፋይናንስ ተቋማት ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ እንደተገዛበትና ቀሪው 100 ሚሊዮን ብር የሼሪዓ መርህን በተከተለ መልኩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሙዳራባህ ኢንቨስትመንት ሂሳብ እንዲቀመጥ መደረጉን ጠቅሰዋል።
መንግስትም መነሻ ካፒታል እንዲሆን ለፈንዱ 200 ሚሊዮን ብር እንደሚመድብ ደንቡ በደነገገው መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር የፈንዱን ስራ ለመጀመር 25 ሚሊዮን ብር መልቀቁን ጠቁመዋል።
መንግስት ፈንዱ ስራውን እንዲጀምር ቢሮ ማደራጀትና ሎጅስቲክስን ጨምሮ ወሳኝ ድጋፍ ማድረጉንና የዓለም ባንክም ለፈንዱ የአቅም ግንባታ ስራዎች መደገፉንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ደስታ፤ ባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ የመውደቅ አደጋ ቢያጋጥም ገንዘቡ ለአስቀማጮች የሚመለስበት አሰራር መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የፈንዱን ገንዘብ ላልተፈለገ አላማ የሚጠቀሙ አካላትም በፈንዱ ማቋቋሚያ ደንብ መሰረት በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ የፈንዱ መጀመር ትልቅ ስኬት እንደሆነና ከለውጡ በኋላ በፋይናንስ ዘርፉ የተካሄዱ ሪፎርሞች ውጤት አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ያቋቋመች 148ኛ አገር መሆኗ በመግለጫው ወቅት ተጠቅሷል።