የብሄራዊ ደህንነት ሥጋት የሆነውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የጋራ ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሄራዊ ደህንነት ሥጋት የሆነውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የጋራ ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የብሄራዊ ደህንነት ሥጋት የሆነውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከልና ለመመከት የጋራ ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር /ኢንሳ/ 4ኛው የሳይበር ደህንነት ወርን ምክንያት በማድረግ ከክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችና ከንቲባዎች ጋር ተወያይቷል።
ከርዕሳነ መስተዳደሮቹና ከንቲባዎቹ ጋር የተደረገው ውይይት በአስተዳደሩ ባለሙያዎች ባለማው "ደቦ" በተሰኘው ቪድዮ ኮንፍረንስ መተግበሪያ አማካኝነት ነው።
በውይይቱም በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በተዘጋጁ ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና አሰራሮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ፤ በኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም 214 የሳይበር ጥቃት መሰንዘሩን አስታውሰው የጥቃት ሙከራው በዓይነትና መጠን ጨምሮ በ2015 ዓ.ም ወደ 6 ሺህ 959 ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።
ይህም የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሁሉንም ትኩረት የሚሻና የብሄራዊ ደህንነት ሥጋት መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለማወቅ በተካሄደ ጥናት 75 በመቶ ያህል ተቋማት ለጥቃት ተጋላጭ መሆናቸው ተመላክቷልም ነው ያሉት።
በመሆኑም ተቋማት ያላቸውን የሰው ኃይል ማብቃት፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማዘመንና ተቋማዊ ደረጃጀቶችን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድ ክልሎች የማይበገር የሳይበር ደህንነት ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ቁልፍ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል።
ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።
የሳይበር ደህንነት ጥቃት ውስብስብ፣ የማይገመት፣ ተለዋዋጭና ድንበር የለሽ በመሆኑ በመንግሥትና በተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብበር ይፈልጋል ብለዋል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፍቅረሥላሴ ጌታቸው፤ በሳይበር ደህንነት ጉዳይ እንደ አገር ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሎች ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ ከወጡ የአሰራር ሥርዓቶች ጋር የተጣጣሙ አሰራሮች ሊኖራቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ እገዛና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።