ዳያስፖራው ባለፉት ሶስት ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ልኳል - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ባለፉት ሶስት ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ልኳል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት ዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ይህን የገለፀው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀሙን ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው ።
ባሳለፍነው ሐምሌና ነሐሴ ወራት ከ500 በላይ የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንቶችን በመክፈት ከ 699 ሺህ ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸውንም ገልጿል።
በሩብ ዓመቱ ከዳያስፖራ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግ በተደረገው ድጋፍና ክትትል ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ በህጋዊ መንገድ ገንዘብ መላኩን አስታውቋል።
የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግም 250 የዳያስፖራ አባላት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ክትትል፣ ድጋፍና የማማከር ስራ ተሰርቷል።
ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘም ከ 89 ሺህ በላይ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትን ያሳተፈና ወቅታዊና ሀገራዊ የልማት ጉዳዮች የተዳሰሱባቸው የበይነ መረብ መድረኮችን እንዳካሄደም ተጠቁሟል።
በዚህም ነባር የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩና አዳዲሶችም እንዲቋቋሙ ድጋፍ መደረጉንና የወጣት ዳያስፖራ አባላትን ሀገራዊ ግንዛቤና ተሳትፎ የሚያሳድጉ ተግባራትም መከናወናቸውን አስታውቋል።
የዳያስፖራ አባላትንና አደረጃጀቶችን በማስተባበርም በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በፋርማሲና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተካሂዷል፡፡
በሚቀጥሉት ጊዜያትም የተጀመሩ አዳዲስ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጠልና ሁሉንም የዳያስፖራ አቅሞች አሟጦ ለመጠቀም መዘጋጀቱን አብራርቷል።
በተለይም በቀጣይ ሩብ አመት የተመረጡ የተሳትፎ ፓኬጆችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ የመቅረፅ፣ የማስተዋወቅና የመተግበር ስራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁሟል።