በኦሮሚያ ክልል የታቀደውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማሳካት ለውሃ አጠቃቀም ትኩረት መሰጠት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የታቀደውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማሳካት ለውሃ አጠቃቀም ትኩረት መሰጠት አለበት
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22 / 2016(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ለማሳካት ለውሃ አጠቃቀም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በክልል ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅት አቶ ሽመልስ፤ በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ባለፉት ሶስት ዓመታት በስፋት ሲሰራበት መቆየቱን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮ ደግሞ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።
ይህንን እቅድ ለማሳካት የክልሉ መንግስት የግብርና ግብዓትን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ለበጋ መስኖ ልማት ውሃ ወሳኝ በመሆኑ የግብርና ባለሙያውም ሆነ አርሶ አደሩ ሀብቱን ባግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱራህማን አብደላ፣ ይህንን የተለጠጠ እቅድ ለማሳካት ሁሉም በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።
ዘንድሮ በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት 105 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ አንስተው ፤እቅዱን ለማሳካት የክልሉ መንግስት በሁሉም መልኩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው ፤ የዘንድሮውን እቅድ ለማሳካት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱን ተናግረዋል።
ከታረሰው መሬት ውስጥም እስከ ዛሬው ድረስ 525 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ላለፉት ሶስት ዓመታት የበጋ መስኖ ልማት ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታዬ ጉዲሳ ናቸው።
ልማቱ ሲጀመር በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደነበረ አውሰተው፤ ዘንድሮ በ105 ሺህ ሄክታር ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አበረታችና ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ተግባር መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል የመኸር አዝመራ በስፋት በተከናወነባቸው አካባቢዎች በኮምባይነር ታግዞ የምርት ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ሰበታ ሀዋስ ወረዳ አዋሽ በሎ አካባቢ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተሳተፉ የሚገኙት አርሶ አደሮች መካከል አቶ ተስፋዬ ጉደታና እጅጉ ተሬቻ ይገኙበታል እሳቸው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው፤ ተጠቃሚነታቸውም እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘንድሮም በዝግጅት ላይ እንደሆኑ አንስተው፤ ከሞተር ፓምፕ ጀምሮ አስፈላጊ ግብዓቶች እየቀረቡላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።