ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ዋነኛ መሰረት አድርጎ በመያዝ መስራት ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የምጣኔ ሃብት ዕድገቱ ዋነኛ መሰረት አድርጎ በመውሰድ በልዩ ትኩረትና ትብብር መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ፈተናዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በንቅናቄው በሀገር ውስጥ ምርቶች ገበያ ላይ የተሻለ መነቃቃት የተፈጠረ መሆኑን  በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየትና መፍትሄ በመስጠት ረገድ አበረታች ጅምሮች መኖራቸው ተነስቷል።

የፌዴራልና የክልል መንግስታት በንቅናቄው ያደረጉት ተሳትፎ አበረታች ቢሆንም ዘርፋ ተወዳዳሪና ለብዙ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንዲችል የበለጠ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በመድረኩ  ተመላክቷል።

የውይይት መድረኩን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደመቀ መኮንን፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት ያስቻለና ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የምጣኔ ሃብት ዕድገቱ ዋነኛ መሰረት አድርጎ በመያዝ በላቀ ትብብርና ጥረት መስራት ይገባልም ነው ያሉት።

በተለይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል በኩል በየደረጃው ያለው አመራር በቁጭትና በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

ከፖሊሲና አሰራር ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት ለነገ የማይባል ተግባር ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት በኩል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለአብነትም በሩብ ዓመቱ በ350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ 360 ያህል ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊው እገዛ ተደርጎላቸው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅስዋል።

በመሆኑም አመራሩ በተለይም የግል ዘርፉ ለዘላቂ ልማትና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ያለውን ሚና በመረዳት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ በፌዴራልና በክልል ደረጃ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቃ የተከናወኑ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው   በስትሪንግ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል ።

በተለይም ምርቶች ላይ እሴት መጨመር፣ የግዥ ስርዓቱን ማዘመንና ጥራት ያለው ምርት ለሀገር ውስጥና ለወጭ ገበያ ማቅረብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የኮሚቴው አባላት ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም