ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር  ኮሚሽን ተባባሪ አካላት ሀገራዊ አንድነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳሰበ

ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- ተባባሪ አካላት ልዩነቶችን በማጥበብና መፍትሔዎችን በማመላከት ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር  እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር  ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ  አዳዬ አሳሰቡ ።

ኮሚሽኑ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተውጣጡና በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ ለሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ዛሬ በሆሳዕና መስጠት ጀምሯል ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን በሰባት ክልሎች በወረዳ ደረጃ ወኪሎች መምረጡንና በክልሎቹ አሳታፊና አካታች ምክክር  ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጉን በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በመፍታት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በዓዋጅ ቁጥር 1265/14 የተቋቋመ ነው።

ኮሚሽነሩ ዶክተር ዮናስ  አዳዬ  በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ምክክር መሰረታዊ አካሄድ ነው።


 

በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ለውጥንና እድገትን ለማስመዝገብና በዜጎች ላይ መተማመንን በማጎልበት ሰላምን ማስጠበቅና ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ምክክር በሰለጠነ መንገድ ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል። 

ኮሚሽኑ እንደ ሀገር ለገጠሙን ችግሮች መውጫ ለማፈላለግ መመስረቱን ገልጸው፣ሀገራዊ ምክክርን ለማመቻቸት የተጠናከረ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ ተባባሪ አካላት በመለየት ግንዛቤ የማስጨበጫ ስልጠናውን ማዘጋጀቱን ዶክተር ዮናስ አስታውቀዋል።

ስልጠናው ለሶስት ቀናት እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም